መስከረም 2013 ዓ/ም ባንካችን አቢሲንያ ለሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውን ቨርቹዋል የባንክ ማዕከል አስመርቆ ሥራ ሲያስጀምር፣ ቴክኖሎጂው ለሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ ለባንክ ኢንዱስትሪው ቀዳሚ ከመሆኑ አኳያ ባንካችንን ፋና ወጊ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ቨርቹዋል የባንክ አገልግሎት ቴክኖሎጂ ደንበኞች የባንክ ቅርንጫፍ የተገደበ የጊዜ ሰሌዳ ሳያሳስባቸው በቅርንጫፍ የሚያገኙትን አገልግሎት በቀን ለ24 ሰዓት በሳምንት ለ7 ቀናት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን፣ ደንበኞች ከሚያገኟቸው አገልግሎቶች መካከል ሒሳብ መክፈት ፣ ገንዘብ ተቀማጭ ወይም ወጪ ማድረግ ፣ ቼክ መመንዘርና ተቀማጭ ማድረግ ፣፤ የሃገር ውስጥ እና የዓለም አቀፍ ሓዋላ አገልግሎት ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፤ እንደ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ካርድ ባንኪንግና ሞባይል መኒ ያሉ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን ለማግኘት ምዝገባ ማከናወን ይገኙበታል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ባንካችን ቴክኖሎጂውን በመላው ሀገራችን ለማስፋፋት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ዛሬ ይፋዊ የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ከተከናወነላቸው 7 ማዕከላት መካከል ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ በሚገኙ የክልል ከተሞች የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት በደሴ፤ በመቀሌ፤ በሆሳዕና፤ በአርባምንጭ ከተሞች ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ ማዕከላቱን 15 አድርሷል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሶስት ማእከላት የምርቃት ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል። ባንካችን በቀጣይ ሳምንታት የሚመረቁ አምስት የሙከራ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ማእከላትን ጨምሮ በመላው ሀገራችን የሚገኙ የቨርቹዋል ባንኪንግ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን 29 በማድረስ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህ ለሀገራችን የባንክ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ የሆነው አይ.ቲ.ኤም. (Interactive Teller Machine) ቴክኖሎጂ ለባንካችን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ደንበኞችም በተለየ ተግባራዊ በማድረግም ባንካችን ቀዳሚ የንግድ ባንክ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ባንካችን አቢሲንያ በሚቀጥሉት ሳምንታት የሙከራ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ተጨማሪ 5 የቨርቹዋል ባንኪንግ ማዕከላትን አስመርቆ ስራ ለማስጀመር በሂደት ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ከተመረቁት ማዕከላት መካከል በቃሊቲ፤ በጎፋ እንዲሁም በጀሞ አካባቢ ይገኙበታል።
Leave a Reply