በኅብረ ብሔራዊ ማንነት የደመቀች ኢትዮጵያ፣ የበርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ናት፡፡ እነዚህ እሴቶችዋ ደግሞ ሀገራዊ ማንነት ከመፍጠር ባሻገር በዓለም ላይ ተለይታ እንድትታወቅ አድርገዋታል፡፡ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ዕሴቶች ካዋለዳቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኛው በዓላት ናቸው፡፡
በዓላት ብሔራዊ ሆነው በዕረፍት ቀናት የሚከበሩ በመሆናቸው ሕዝቦች አምረውና ደምቀው የሚታዩባቸው፤ ከመቼውም ጊዜ በላይ አጊጠውና ተውበው የሚያሳልፉበት ነው፡፡ አሮጌው በዐዲስ የሚቀየርበት፤ የሚበላ፣ የሚጠጣ የሚትረፈረፍበት፤ ወዳጅ ከዘመድ እንኳን አደረሳችሁ እያለ የሚጠያየቁ ናቸው፡፡
በዓመት ዓመት መምጣታቸውን በጉጉት እየጠበቅን የምናከብራቸው በዓላት፣ ዕለቱን ለማሳለፍ የምናደርጋቸው ነገሮች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የምናወጣው ወጪ ደግሞ ያለስስት ነው፡፡ አንዳንዱ ዓመት የቋጠረውን ጥሪት ይፈታል፤ ሌላው ተበድሮ ጭምር ያሳልፋል፤ አንዳንዶች ካላቸው ቀንሰው ያከብራሉ፤ ብልሆች ደግሞ ቀድመው ለበዓል በቆጠቡት ገንዘብ በዓሉ ከሚሰጠው ደስታ በላይ በሙሉ ልብነት ሳይቸገሩ ያሳልፋሉ፡፡ እነሆ ብልሆች በዓላትን እንዴት በመቆጠብ እንደሚያሳልፉ ምሥጢራቸውን እንገራችሁ፡፡
፩. የበዓል በጀት ያዘጋጁ
በዓላት የሚፈጥሩት ስሜት ከፍተኛ ነው፡፡ ዕለቱ ከምግብና መጠጥ ጋር ተዳምሮ ደስታችን እጥፍ ያደርጉታል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ የማንቆጣጠራቸው ብዙ ናቸው፡፡ አንደኛ ወጪ ነው፡፡ ለመጋበዝ፣ ለመሸመት፣ ቤተሰቦቻችን ለመጠየቅ የምናወጣቸው ወጪዎች ከዕቅድ በላይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ከበዓል በኋላ ያለውን ኑሮአችንን ያዛባዋል፡፡ ይንንን ለማስተካከል በቅድሚያ ለበዓል ብቻ የተለየ በጀት ይኑርዎ፡፡ አንዳንድ አስተዋዮች ለበዓል ሰሞን ቀድመው በመቆጠብ ያለጭንቀት ወጪና ገቢያቸውን ያመጣጥናሉ፡፡ ስለዚህ እርስዎም ይህንን ይሞክሩት፡፡
፪. ለበዓል የሚገዙትን ነገሮች ለይተው ያኑሩ
በጀት የተመጣጠነ ገቢና ወጪ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በልዩ ሁኔታ ለበዓል የቆጠቡትን ገንዘብ ምን ምን ላይ እንደሚያውሉ ውሉን መሳት የለበትም፡፡ ስለዚህ የቆጠቡትን ገንዘብ አመዛዝነው እንዲጠቀሙ ቀደም ብለው የሚፈልጓቸውን እና የሚገዟቸውን ነገሮች በዝርዝር ያስቀምጡ፡፡ መግዛት የሚፈልጉትን ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱ ምን ያህል ማውጣት እንደሚችሉ ይወቁ። ዝርዝሩ ከበጀቱ በጣም የሰፋ ከሆነ የወጪ መጠኑን ሊቀንስ በሚችል መልኩ እንደገና ይከልሱ፡፡
፫. ባዘጋጁት ዕቅድና ዝርዝር መሠረት ቀደመው ይግዙ
በሀገራችን ልማድ መሠረት በበዓላት ወቅት የዋጋ ንረት ይፈጠራል፡፡ ግብይቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ስለሚፈጥኑ ከነበረው ዋጋ ከእጥፍ በላይ ይጨምራሉ፡፡ ስለዚህ አንደኛው መፍትሔ በዝርዝሩ መሠረት ለበዓል የሚፈልጉትን ቀደም ብለው መግዛት መጀመር ነው፡፡ ይህም የበዓል ወጪን ቀላል ያደርገዋል፡፡ መጠንቀቅ የሚገባዎ ደግሞ በመጨረሻው ሰዓት ላይ መሸመት መጥፎ አጋጣሚ መሆኑን ነው፡፡ አንድም እንዳያስቡና እንዳያመዛዝ በማድረግ በፍጥነት እንዲወስኑ ያስገድዳል፡፡ ስለዚህ ቀድሞ መግዛትን ልምድዎ ያድርጉ፡፡
፬. ያቀዱትን ገንዘብ ብቻ ይጠቀሙ፡፡
በዓላትን ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመሔድ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከወዳጆችዎ ጋር ሊያሳልፉ ይችላሉ፡፡ በቆይታዎ ቀድመው በተዘጋጁበት እና ኪስዎ ባለው ልክ ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ ምናልባት የካሽ እጥረት ቢገጥምዎ የኤቲኤም ካርድ በመጠቀብ ገንዘብ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከዕቅድዎ በላይ በመሆን በጀትዎን ያዛባዋል፡፡ ስለዚህ በበዓል ወቅት ያቀዱትን ገንዘብ ብቻ ይጠቀሙ፡፡
፭. ገንዘብ በማያስወጡ ጨዋታዎችና መዝናኛዎች በዓልን ያሳልፉ
በዓላትን አስታክከው የሚከወኑ የተለያዩ ሁነቶች አሉ፡፡ ባህላዊ ጨዋታዎች፣ መዝናኛዎች እና ዝግጅቶች በበዓላት ወቅት የሚከወኑ ሁነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ መዝናኛዎች ምንም ወጪ የማይጠይቁ ከክፍያ ነጻ የሆኑ ናቸው፡፡ ካላቸው ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ፋይዳ አንጻር ሲታይ ደግሞ እጅግ የሚያደስቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የገና ጨዋታ ተጠቃሽ ነው፡፡ አሁን አሁን ደግሞ በተለያዩ የቴልቪዥን ጣቢያዎች የመዝናኛ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ ስለዚህ በዓላትን በእንደነዚህ ሁነቶች ማሳለፍ ገንዘብ እንድንቆጥብ ይረዳናል ማለት ነው፡፡
ብልሆች ለተሻለ ነገ በማሰብ ዛሬ ይቆጥባሉ፡፡ ለመቆጠብ ደግሞ ምክንያት ሳይሆን ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡ ትጉኃን ለውጥን ዛሬ ላይ ትንሽ ጠጠር በማኖር ነጋቸው ይገነባሉ፡፡ አቢሲንያ ባንክ ከለውጦ ጎን በመሆን እየደገፈ ዐብሮት ይዘልቃል፡፡
ምኒልክ ብርሃኑ
Leave a Reply