ባንካችን በቅርቡ ያስተዋወቀውን የPayment Gateway Technology በመጠቀም በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የእጅ ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው በቀላሉ ገንዘብ መላክ የሚችሉበት መንገድን ፈጥሯል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሕዝብና የመንግስት ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ በሚዘጋጁ የተለያዩ የድጋፍ ማሰባሰብያ ፕሮግራሞች ላይ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቀላሉ ለሀገራቸውም ሆነ ለወገናቸው መድረስ የሚችሉበት ሁኔታ በአቢስንያ ባንክ በኩል ተመቻችቷል፡፡ CashGo የተሰኘውን ይህን አዲስ የስልክ መተግበሪያ ማንኛውም ሰው በቀላሉ ከPlayStore ወይም AppStore በማውረድ የቪዛና ማስተር ካርዱን ተጠቅሞ ለቤተሰብ እና ለወዳጅ ዘመዱ ሲያሻው ገንዘብ በመላክ ፣ ሲያሻው ደግሞ ለሚፈልገው ድርጅት አልያም ፕሮጀክት በቀላሉ ድጋፍ ማድረግ ያስችለዋል፡፡አቢሲንያ ባንክ ይህ በአይነቱ ለየት ያለ አገልግሎትን የሚሠጥ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሲያደርግ ፣ለሀገራችንም ሆነ ለመላው ህብረተሰብ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በዋነኛነት የውጭ ምንዛሪ የማግኘት አቅምን በእጅጉ ያሳድጋል፣ ገንዘብ ወደ ሀገር ውስጥ ለመላክ ለሚያስብ ከሀገር ውጪ ለሚኖር ሰው ከሌሎች የሐዋላ መላኪያ ዘዴዎች በተሻለ በቀላል ዘዴና በአነስተኛ ዋጋ ገንዘብ መላክ እንዲችል ያበረታታል፣ ከዚህም ባለፈ በኢ-መደበኛ መንገድ የሚደረገውን የሐዋላ ዝውውር ለመቀነስ የሚደረገውን የመንግስትን ጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ያግዛል፡፡በሀገራችን በርካታ የልማት ሀሳቦች በመንግሥትና በተለያዩ አካላት ተነድፈው ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ቢኖርም ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ከሀገር ውጪ ለሚኖሩ ወገኖች የተመቸ የገንዘብ መላኪያ አማራጭ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ ምክንያት አመርቂ የሆነ የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል ለሚባለው ጉዳይ ይህ የሞባይል መተግበሪያ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ፍላጎቱ ላላቸው ከሀገር ውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
Leave a Reply