ባንካችን አቢሲንያ በቀን ለ24 ሰዓታት በሳምንት ለ7 ቀናት (24/7) ዓይነ ስውራን ደንበኞችን ማዕከል ባደረገ መልኩ አገልግሎት የሚሰጥ በድምጽ የታገዘ የኤ.ቲ.ኤም. አገልግሎት ጀመረ፡፡ ለሀገራችን ኢትዮጵያ እንዲሁም ለባንኪንግ ኢንዱስትሪው ይኸን አዲስ አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ ባንካችን አቢሲንያ ቀዳሚ ነው፡፡
ባንካችን አቢሲንያ የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅዱን ሲነድፍ ለደንበኞች ምቾቱን የጠበቀና የላቀ የባንክ አገልግሎት (Excellent Banking Services) ለመስጠት በተለየ ሁኔታ ለዲጂታል ስርዓት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በዚህም ባንካችን አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ በስትራቴጂክ ዕቅዱ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ አቢሲንያ ኦንላየን፣ ኢ-ኮሜርስ፣ ቨርችዋል ባንኪንግ፣ ፔይመንት ጌትዌይ ያሉ የባንክ አገልግሎቶችን ለደንበኞች እና ለባንክ ማኅበረሰቡ አስተዋውቋል፡፡ በተጨማሪም፣ ባንካችን በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የባንክ ቅርንጫፎች በመክፈት ለማኅበረሰባችን ይበልጥ ተደራሽ ከማድረጉ ባሻገር የኤ.ቲ.ኤምና የፖስ ማሽኖችን ቁጥር በማሳደግ ረገድም አጥጋቢ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
ባንካችን አቢሲንያ በዛሬው ዕለት ዓይነ ስውራን ደንበኞቹን ማዕከል ባደረገ መልኩ የተለያዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችላቸውን በድምጽ የታገዘ የኤ.ቲ.ኤም. የባንክ አገልግሎት አሠራርን በይፋ ጀምሯል፡፡ ደንበኞች ይህን ደህንነቱ የተጠበቀ የባንክ አገልግሎቱን ለማግኘት የኤ.ቲ.ኤም. ካርዳቸውን በማስገባትና በኤ.ቲ.ኤም. ላይ በሚገኘው የድምጽ ማዳመጫ ቦታ ላይ የጆሮ ማዳመጫ (Earphone) በማድረግ የተዘጋጁ መመሪያዎችን እና ምርጫዎችን በመከተል የሚፈልጉትን የባንክ አገልግሎቶች ማግኘት ይችላሉ። በዚህ በድምጽ በታገዘ የኤ.ቲ.ኤም. የባንክ አገልግሎት ዓይነ ስውራን ደንበኞች ያለ ምንም ረዳት (Guardian) ራሳቸውን በራሳቸው የባንክ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችላቸው አሠራር ነው፡፡ በዚህ አገልግሎት ደንበኞች ገንዘብ ወጪ ማድረግ፣ ገንዘብ ከሒሳብ ወደ ሒሳብ ማስተላለፍ፣ የሚስጢር ቁጥር መቀየር፣ አጭር የሒሳብ መግለጫ ማተም እና ገንዘብ ወደ ቴሌ ብር መላክ ያስችላቸዋል፡፡
አገልግሎቱ በአማርኛ፣ እንግሊዘኛ፣ ኦሮሚኛ እና ትግርኛ ቋንቋዎች የቀረበ ሲሆን፣ ዓይነ ስውራን፣ ማንበብ የማይችሉ ሰዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ ምክንያቶች የማየት አቅማቸው የደከመ ሰዎች ከሌሎች የኤ.ቲ.ኤም. ካርድ ተጠቃሚዎች እኩል የተሟላ አገልግሎት በመረጡት ቋንቋ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይኸን አገልግሎት ለመጠቀም የአቢሲንያ ባንክ ካርድ፣ የሌሎች ባንኮች ካርዶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ካርዶች (እንደ ማስተር ካርድ፣ ቪዛ ካርድ እንዲሁም ቻይና ዩኒየን ፔይ ካርድ) የያዘ ማንኛውም ግለሰብ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል።
በአገራችን ዓይነ ስውራንን ጨምሮ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኛ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚኖሩ የሚገመት ቢሆንም በባንኪንግ ኢንዱስትሪው በሚፈለገው አግባብ ተደራሽና አካታች (Financial Services Inclusion) በማድረግ ረገድ እምብዛም ትኩረት እንዳልተሰጣቸው ባንካችን ይገነዘባል፡፡ በመሆኑም በዛሬው ዕለት ባንካችን በይፋ ያስመረቀው ይህ አዲስ የባንክ አገልግሎት የዚሁ ተግባር አንድ ርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ አገልግሎቱም ለዓይነ ስውራን ደንበኞች የራሱ የሆነ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡
አቢሲንያ ባንክ ለአምስት ዓመታት በቀረጸው ስልታዊ ዕቅድ መሠረት በቀጣይ ዓመታት አዳዲስ ደንበኞችን ለመሳብና ከነባር ደንበኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለመቀጠል ይህን አገልግሎት በአዲስ አበባና በክልል ዲስትሪክት ጽ/ቤቶች በስፋት ለማዳረስ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል፡፡
ባንካችን አቢሲንያ እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያማከለ ሌሎች ተጨማሪ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ሥራውን በቀጣይ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
Leave a Reply