በአለማየሁ ስሜነህ እና ሰብለ ከበደ
አቶ ተካልኝ ገዳሙ ከባንካችን መሥራቾች አንዱ ሲሆኑ፣ የባንካችን የመጀመሪያ ፕሬዚደንትና እንዲሁም የቦርድ አባል የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ከ11 ዓመት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከሚኖሩበት አሜሪካን ሀገር ለአጭር ጊዜ እረፍት በመጡበት ጊዜ (ከጥቂት ወራቶች በፊት)፣ ስለ ባንካችን ጠቃሚ ታሪካዊ መረጃ ሊሠጡን መልካም ፈቃዳቸውን አግኝተን ከአረፉበት ሒልተን አዲስ አበባ ሆቴል ተገኝተን አነጋግረናቸው ነበር፡፡ በቆይታችንም በርካታ ጉዳዮችን (የባንካችን ምስረታ እና ተያያዥ ታሪኮች፣ በወቅቱ ስለነበረው የባንክ ዘርፍ ቅርፅ፣ ከእዛ በፊት ስለነበሩ ድንቅ የባንክ ባለሙያዎች፣ ስለባንክ ሙያ፣ ስለ ድርጅት ባህል፣ ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ስለነበረው ስቶክ ኤክስቼንጅ ገበያ (Stock Exchange Market)፣ አሁን ላይም አሜሪካን ሀገር ስለመሠረቱትና ስለሚያስተዳድሩት በአሜሪካ የመጀመሪያው የዲያስፖራ ባንክ…እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች) አንስተንባቸው ብዙ አጫውተውናል፡፡ ከእዛ ውስጥ አቶ ተካልኝ ገዳሙ ማን ናቸው ከሚለው ጀምሮ፣ የባንካችን ቅድመ ታሪክ ጋር የሚያያዘውን የተወሰኑትን እንደሚከተለው ለማጋራት ወደድን፡፡
ጥያቄ፡ አቶ ተካልኝ ገዳሙ እንኳን ወደ ሀገርዎ በሰላም መጡ፣ ከአሜሪካን ሀገር ለአጭር ጊዜ ቆይታ በመጡበት በዚህ ወቅት ጊዜዎን አብቃቅተው ስለባንካችን ጠቃሚ መረጃ እንዲኖረን፣ የባንካችን ታሪካዊ ዳራ እንዲያጫዉቱን ፈቃደኛ ሆነው በመገኘትዎ እጅግ ተደስተናል፡፡
መልስ፡ ከጥያቄአችሁ በፊት እኔም ዕድል ይሰጠኘና፤ በዚህ አጋጣሚ በምታቀርቡት ጥያቄ መልስ በመስጠት መረጃ አንድ አስተዋፅኦ እንዳደርግ ስለጋበዛችሁኝ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
ጥያቄ፡ ስለረጅም የሕይወት ጉዞዎ፣ መቼና የት እንደተወለዱ፣ አስተዳደግዎ፣ የሥራ ህይወትዎ እንዲሁም የትምህርት አፈፃፀምዎ ምን እንደሚመስል በአጭሩ ይግለፁልን?
መልስ፡ ኦሆ! ይሄ የሰማይ ስባሪ የሚያህል ጥያቄ ነው፡፡ ቶሎ በአጭሩ መመለስ ያስቸግረኛል፣ ልሞክር፡፡ እኔ እንግዲህ የተወለድኩት በእኛ አቆጣጠር በ1926 ዓ.ም. ነው፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን ሊወር ሁለት ዓመት ሲቀረው እንደማለት ነው፡፡አሁን እንግዲህ ይኸው 86ኛ ዓመቴን ጨርሼ 87 ሊሄድ ነው፡፡ የተወለድኩት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጎሬ የምትባል ከተማ ነው፡፡ ከዚያ የመጀመሪያ ትምህርቴን ያጠናቀኩት እዚያ ነው፣ በዚያ ጊዜ በጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍለ ሀገሮች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ስለሌሉ ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ ወደ አ.አ. ይመጡና በመንግሥት ወጪ አዳሪ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ይገባሉ፡፡ እና ያኔ እኔ እንደማስታውሰው በእኛ አቆጣጠር በ1940 ዓ.ም. አ.አ. መጥቼ ዳግማዊ ምንሊክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዲስ መቋቋሙ ነው፣ ከተለያየ ከተማ ከመጡ ተማሪዋች ጋር አንድ ላይ የመጀመሪያዎቹ ሆነን ገባን፡፡
ከዚያ ስንጨርስ ዪኒቨርስቲ ኮሌጅ የሚባል ነበር ያን ጊዜ የ4 ዓመት ኮርስ ተከታትለን የባችለር ዲግሪ አገኘን፡፡ አሁን ደግሞ በመንግሥት ኪሳራ ውጭ ሀገር ተልከን እኔ ኢኮኖሚክስ ተምሬአለሁ፡፡ እዛ እንዳለሁ ትምህርቴን ስጨርስ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ተቀጠርሁ፡፡ ስምንት ዓመት እዚያ ሠራሁኝ (ይህም ከፊሉን UN, Newyork በተቀጠርኩበትና የተቀረውን አዚህ ECA, Addis Ababa)፡፡ ስምንተኛ ዓመቴን እንደጨረስኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሃ/ወልድ ሀገርህን ማገልገል አለብህ ብለው የመንግሥት ሥራ ውስጥ እንድገባ አደረጉ፡፡ መጀመሪያ የዛን ጊዜ ፕላንና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ነበር የሚባለው፣ አቶ ሐዲስ አለማየሁ ነበሩ ሚኒስትሩ፣ በእርሳቸው ስር ፕሮጀክትን እያዘጋጀ የልማት በጀት የሚያቀርብ አንድ ድርጅት ነበረ፡፡ ትንሽ እዛ እንደሠራሁ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆንኩኝ፡፡ እዛ ሁለት ዓመት ከሠራሁ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ውጪ ሀገር ሄጄ ተመለስኩ፡፡ የፕላንና ልማት ኮሚሽን የሚባለው አቶ ሐዲስ አለማየሁ ከሄዱ በኋላ የፕላን ኮሚሽን ተባለ እኔም የፕላን ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆንኩኝ፡፡
ከዚያ እንደምታውቁት አንድ ሶስት አራት ዓመት ከሠራሁ በኋላ አብዮቱ ፈነዳ (ተቃጠለም የሚሉ አሉ)፣ በ1966 ዓ.ም. መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ለአንድ ዓመት ያህል ከጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ጋር ሠራሁ፡፡ ብዙ ችግር ስለነበረ እኔም ስላልተመቸኝ አሰናብቱኝ ብዬ ደብዳቤ አስገብቼ አሰናበቱኝ፡፡ ከዚያ በኋላ አፍሪካ ልማት ባንክ አስራ ስድስት ዓመት ተኩል ሠራሁኝ፡፡ ከእዛ ከተመለስኩ በኋላ ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆነን አቢሲንያ ባንክን አቋቋምን፣ ከማስታውሳቸው ሰዎች መካከል ከመጀመሪያ አቶ ደበበ ሐብተ ዮሐንስ፣ አቶ ኃይሉ ሻውል፣ ጀነራል ታፈሰ አያሌው የሚባል በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የኢትዮጵያ አየር ሐይል ጀነራል የነበረ ሆነን ሥራውን ጀመርን፡፡ እዚህ አንድ ስድስት ሰባት ዓመት ከሠራሁ በኋላ አሜሪካን ሀገር ተመልሼ ይኸው 11 ዓመት እዛ ቆይቼ ለመጀመሪ ጊዜ መመለሴ ነው፡፡ ይሄ ነው እንግዲህ በአጭሩ፡፡
ጥያቄ፡ በጣም እናመሰግናለን፡፡ UN, Newyork እንዲሁም ECA, Addis Ababa ከዛም በኋላ በነበርዎት ኃላፊነት ሲቀጠሩ፣ ሥራዎችን የተቀላቀሉት፣ አመልክተው በውድድር ሳይሆን፣ እርስዎን የሚያውቁ ሰዎች ጠቁመዎት ወይም (Recommend) አድርገዎት እንደሆነ ሰምተናል፣ እስቲ ስለዚህ ዝርዝሩን ያጫውቱን፡፡
መልስ፡ አዎ! በመሠረቱ ዕውነት ነው፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልጀምርና፣ አሜሪካን ሀገር ተማሪ ቤት እንዳለሁ የማስተርስ ዲግሪ በኢኮኖሚክስ ለማግኘት ተምሬ ልጨርስ ስል፣ አንድ ቀን የእኔ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሠር ይጠራኝና ከተባበሩት መንግስታት አንድ ደብዳቤ ደርሶኛል፣ በኢኮኖሚክስ መስክ የሚመረቁ ጥሩ ጥሩ የሆኑ የአፍሪካ ተማሪዎች እንዳሉ ከእነሱ መርጠህ ስማቸውን ላክልኝ ተብያለሁ፣ እናም የአንተን ስም ልልክ ነው አለኝ፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ማለት የሀገር መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሰብስበው ዲስኩር የሚያደርጉበት፣ ሲጋጩ የሚውሉበት ነው፣ እናም እኔ ከየተባበሩት መንግስታት ጋር ምንም ጉዳይ የለኝም፡፡ አይ ተሳስተሃል፣ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ልዩ ልዩ ክፍሎች አሉ፣ ከነዚህም አንዱ የኢኮኖሚ ክፍል ነው፡፡ እዛ ብትሄድ ጥሩ ልምድ ታገኛለህ አለኝ፡፡ እኔ እንዲህ ያለ ሐሳብ የለኝም ፣ ይህን ትምህርት ስጨርስ ሳልውል ሳላድር በቀጥታ ወደ ሀገሬ መሄድ ነው የምፈልገው፣ መንግሥት ነው ያስተማረኝ እና የተማርኩበትን ወጪ ትንሽም ቢሆን ለማካካስ እፈልጋለሁ፣ ደግሞ ግርማዊ ንጉሰ ነገሥት ወደዚህ ሀገር ስመጣ ሲሸኙኝ፣ በሉ ተምራችሁ ተመልሳችሁ ሀገራችሁን አገልግሉ ብለዋል፡፡
ሀገሬን፣ ተመልሼ ማገልገል ነው የምፈልገው፣ ብዬ ትንሽ ተከራከርኩኝ፡፡ አንተ ምን አስጨነቀህ፣ እኔ ስምህን ልላክ ካልፈለግክ እኔ አልፈልግም በላቸው፣ የሚያስገድድህ የለም አለኝ፡፡ ደግሞም ብታስተውል ለየተባበሩት መንግሥታት መሥራት ማለት ለኢትዮጵያ መሥራት እንደማለት ነው፡፡ የአንተ ሀገር እኮ ይህንን የተባበሩት መንግሰታት ድርጀትን ከአቋቋሙት ሀገሮች መካከል በቅድሚያ የምትነሳ ናት፡፡ የእናንተን ሀገር ታሪክ አውቃለሁ፣ ስለዚህ ኢትዮጵያን እንደ መርዳት ነው፡፡ አይ እኔ ምንም አልጣመኝም አይሆንም አልኩት፣ ግን ተጫነኝ፣ ሲጫነኝ ከጭቅጭቁ ለመገላገል በል እንግዲህ ላከው አልኩት፡፡ ከሁለት ወር በኋላ ከየተባበሩት መንግስታት ደብዳቤ ይደርሰኛል፡፡ ትምህርትህን ስትጨርስ ጥቂት ሳምንታት ሲቀሩህ ደውልልኝ ወይም ደብዳቤ ላክልኝ የሚል ነበር፡፡ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ ስል፣ ያን ጊዜ ትምህርታችንን ስንጨርስ እንደምናደርገው፣ ዋሽንግተን ዲሲ ላለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ የትምህርት ክፍል አታሼ ሐላፊ ትምህርቴን መጨረሴንና ወደ ሀገሬ የምመለስበትን ትኬት እንዲሁም በዛ ጊዜ የምትሰጥ የኪስ ገንዘብ ነበረች እሷንም ጨምሮ እንዲልክልኝና ጓዜን የምልክበትን ሁኔታ እንዲያመቻችልኝ ፃፍኩለት፡፡
ያው የተለመደ ነገር ስለሆነ ወዲያው እኔ ከነበርኩበት ቺካጎ Chicago አካባቢ University of Illinois, Urbana chanpaign ከምትባል ትንሽ ከተማ በ Newyork አድርጎ እንዲሁም በእንግሊዝ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባ የአውሮፕላን ትኬት ከእቃ አጓጓዥ ድርጅት ስም ጋር ላከልኝ፡፡ ስለዚህ የምመለሰው በ Newyork በኩል እንደመሆኑ Colombia University, Newyork ይማር የነበረ ሙሉጌታ ወዳጆ የሚባል ወዳጄ ወደ ኢትዮጵያ መመለሴ ነው፣ ስመለስ ደግሞ በNewyork በኩል ስለሆነ አንተ ዘንድ አንድ ሁለት ሶስት ቀን አድራለሁ አልኩት፣ በጣም ደስ ይለኛል ና አለኝ፡፡ እዛ እንደደረስኩ የተባበሩት መንግስታት ጉዳይን አነሳሁበት፣ እንዲህ ያለ ወረቀት ልከውልኛል፣ ምን ይመስልሃል አልኩት፣ ጠይቃቸው ደስ ካለህ ትቀበላለህ ደሰ ካላለህ ትመለሳለህ አለኝ፡፡ እኔም የተባበሩት መንግሥታት መሥሪያ ቤት ሄድኩኝና እንደአጋጣሚ ደብዳቤውን የጻፈችውን ሴትዮ አገኘኋት፣ ደብዳቤውንም አሳየኋት፡፡ ኢንተርቪው ልናደርግህ ነው አለችኝ፡፡ እኔ ለኢንተርቪው ጊዜ የለኝም፣ ብዙ ገንዘብም ስለሌለኝ እዚህ ብቆይ ሁለት ሶስት ቀን ነው፣ ወደ ሀገሬ እየተመለስኩ ነው፣ እግረ መንገዴን ምንድን ነው ብዬ ለመጠየቅ ነው የመጣሁት አልኳት፡፡ እሷም ጉዳዩን በአጭሩ አስረዳችኝ፣ የተባበሩት መንግስታት የኢኮኖሚ ዲፓርትመንቱ እንደ አንተ ያሉ ወጣት ኢኮኖሚስቶችን ይፈልጋል፡፡
በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ECA የሚባል አንድ ትልቅ ድርጅት ይቋቋማል፣ ብትፈልግ እዛ ትሠራለህ፣ እኛ ጋርም ብዙ የአፍሪካ ኢኮኖሚስቶች ስለሌሉንና የአፍሪካ ኢኮኖሚስት ስለምንፈልግ እኛ ጋር ትሠራለህ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢንተርቪው አዘጋጅቼ እነግርሀለው አለችኝ፡፡ ኢንተርቪው የሚያደርጉ አንድ አራት አምስት ሰው በሚቀጥለው ቀን አዘጋጅታ፣ ኢንተርቪው ተደረግኩኝ፡፡ ብዙዎቹን ጥያቄዎች አሁን ላይ አላስታውሳቸውም፣ በዕውነት፣ አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ግን አስታውሳለሁ፣ ብዙ ጥያቄዎች ከጠየቁኝ በኋላ፣ አሁን አንተ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ብትቀጠር፣ የምታገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ፣ ከነዚህም መካከል አንዱ የህይወት ኢንሹራንስ የሚባለው ነው፣ እንግዲህ አንድ አደጋ ደርሶብህ ከዚህ ዓለም በሞት ብትለይ ገንዘቡ ለማነው የሚሄደው? ለአባትህ፣ ለእናትህ …አሉኝ፣ አይ እንዲህ ያለ ነገር ካለ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት፣ ለትምህርት ሚኒስትር ይሂድልኝ አልኳቸው፡፡ አባት እናት የሉህም፣ አሉኝ አልኳቸው፣ ወንድም እህት ዘመዶች የሉህም፣ ወንድም እና እህት የሉኝም ግን ያሉኝ ዘመዶቼ ራሳቸውን የቻሉ ናቸው፣ ይህ የእኔ ጥቅማ ጥቅም አያስፈልጋቸውም፣ ይህ የሚያስፈልጋቸው የኢትዮጵያ ህጻናት ናቸው፡፡ እኔ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እስከ አሁን ያስተማረኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፣ በነጻ ማለት ነው፣ እኔ ደግሞ የአቅሜን ያህል አንድ አይነት አስተዋፅኦ ማድረግ ስላለብኝ ይህ ገንዘብ ሄዶ አንድ ተቋም ተቋቁሞ ወይም ደግሞ ትምህርት ሚንስትር ተማሪዎችን ውጪ እየላከ ሲያስተምር ሊጠቀምበት ይችላል አልኳቸው፡፡ዝም አሉ፡፡ በማግስቱ ተደውሎ ተቀጥረሃል ተባልኩኝ፡፡እኔ አሁን ሳስብ እነዛን ጥያቄዎች መልሼ ይሆናል፣ አይሆንም፣ ግን በጣም የመታቸው ግን ይህ መጨረሻ ላይ የሰጠሁት መልስ ይመስለኛል፡፡ ከዛ ሥራ ጀመርኩ፡፡ ሥራ የመጣልኝ ተማሪ ቤት ሳለሁ ነው ለማለት ይቻላል፡፡
እዚህ 8 ዓመት ካገለገልኩ በኋል፣ ፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃ/ወልድ ይፈልጉሃል ተብዬ ቢሮአቸው ሄጄ፣ ለምንደነው አንተ ሀገርህን የማታገለግለው ብለው ከአቶ ሐዲስ አለማየሁ ጋር እንድሠራ ቅድም እንደጠቀስኩት አሾሙኝ፡፡ አንድ 9 ዓመት እንደሠራሁ፣ በ10ኛው ዓመት ደርግ መጣ፣ጥቂት እንደሠራሁ ተሰናብቼ ቁጭ አልኩኝ፣ ከእዛ ደግሞ ከአፍሪካ ልማት ባንክ አንድ ወረቀት ይመጣል፣ ለአፍሪካ ልማት ባንክ አዲስ ፕሬዚዳንት ተሹሟል፣ የእሱ የኢኮኖሚ አማካሪ እንድትሆን እንፈልጋለን ይላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሥራ ነው የምትሠራው፣ ደሞዙ ይህን ያህል ነው ይላል፡፡ እንዴ ምንድን ነው ይሄ፣ እርግጥ ሥራ አፈልጋለሁ፣ ግን አልጠየቅኳቸውም ብዬ አንድ አሁን ስዊዲን የሚገኝ በላቸው አስራት የተባለ ወዳጄን፣ እንዲህ ኣይነት ጥያቄ መጣ፣ ምን ልበላቸው ስለው፡፡ አይ አንተ ደግሞ የማይጠየቅ ጥያቄ ነው የምትጠይቀው፣ አሰናብቱኝ ብለህ ከደርግ ወጥተሃል፣ ደሞዝና ሥራ አሁን የለህም፣ ዝም ብለህ ሂድ፣ ከሆነ ሆነ ካልሆነ ሌላ ቦታ ትሄዳለህ አለኝ፡፡ ዕውነቱን ነው ብዬ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሄድኩኝ፡፡ ፕሬዚዳንቱን አገኘሁት፣ ነገር ግን በምን ምክንያት የቅጥር ኮንትራት ወረቀት እንደተላከልኝ አልነገረኝም፡፡ እንደምገምተው ግን ሰዎች የእኔን ስም ሰጥተውት እንደሚሆን ነው፡፡
እዛ 16 ዓመት ተኩል ያህል ከሠራሁ በኋላ፣ ከሀገር ውጪ ከዚህ ጊዜ በላይ መቆየትም ስለሰለቸኝ ጭምር፣ ወደ ሀገር መመለስ አለብኝ ብዬ ተመለስኩ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሰመለስ ደግሞ እነ አቶ ሐይሉ ሻወል፣ አቶ ደበበ ሐ/ዮሐንስ፣ ጀነራል ታፈሰ አያሌው ባንክ ልናቋቋም ነውና እባክህ አብረን እንሥራ ተቀላቀለን አሉኝ፡፡ አሁን ጡረታ ላይ ነኝ፣ ነገር ግን አንድ የታሪክ ማስታወሻ ለመፃፍ እንዲሁም በየጊዜው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የሚያጠና ፈረንጆቹ Think Tank የሚሉትን የኢኮኖሚ ጥናት ድርጅት ማቋቋም እፈልጋለሁ በማለት ትንሽ ተከራከርን፣ ተጫኑኝ ለማለት አችላለሁ፣ መቼም ሰው ሲጫነኝ እምቢ ማለት ትንሽ ያስቸግረኛል፡፡ ለሀገራችን የሚያስፈለግ ነው እያሉ ነበር የሚነግሩኝ፣ ይህን ደግሞ አለመቀበል ማለት ሀገሬንም ህዝቤንም አላገለግልም እንደማለት ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ይህን ሥራ ለአንድ ዓመት ከሠራሁ በኋላ የማስበውን ሥራ ከዚያ በኋላ እሠራለሁ ብዬ ኃላፊነቱን ተቀበልኩ፡፡
ያላችሁት ነገር ዕውነት ነው፣ እስከአሁን ተቀጥሬ የሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶች ሁሉ የእኔን ስም አየሰሙ ዕድሉን የሰጡኝ ናቸው፡፡ አሁን ደግሞ እንደ አጋጣሚ አሜሪካን ሀገር የዛሬ 11 ዓመት ስመለስ፣ እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን አዲስ ባንክ ማቋቋም እንፈልጋለን ብለው ኃላፊነቱን እንድቀበል ጠየቁኝ፣ በዚህም ጥያቄ ተሸንፌ እሺ ብዬ ተቀበልኩ፡፡ አሁን ላይ እሱን በመሥራት ላይ ነው ያለሁት፣ ይሄንን እንደ ዕድል ነው የምቆጥረው፡፡ የእኔ ረጅም የህይወት ጉዞ ይህን ይመስላል፡፡
ጥያቄ፡- አቢሲንያ ባንክን ከመሥራችነት አንስቶ፣ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት በመሆን፣ እንዲሁም በቦርድ አባልነት ወደ 7 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከዚህ ተነስተን ባንካችን ከተመሠረተ 25 ዓመት ሊሞላው እንደ መሆኑ፣ አቢሲንያ የሚለው የባንካችን ስያሜ እንዴት እንደመጣ ታሪካዊ ዳራውን ቢያጫውቱን፡፡
መልስ፡- እኔ እንግዲህ ከእነ አቶ ደበበ ኃ/ዮሐንስ እና ኢንጂነር ሐይሉ ሻውል ጋር ከመቀላቀሌ በፊት ባንኩን የማቋቋም ሥራ ተሠርቶ ነበር፡፡ ባንኩን ለማቋቋም የተነሱት ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ቀድመው ካፒታል አሰባስበውም ነበር፡፡ የባንኩንም ስም መርጠውና ሰይመው ነው እኔ የተቀላቀልኩት፡፡ ‹‹አቢሲንያ›› ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ንግድ ባንክ መጠሪያ ነበር፣ በአፄ ምንሊክ ዘመን የተቋቋመ ነው፡፡ ያቋቋሙት ደግሞ እንግሊዞች ናቸው፡፡ እንግሊዞች ያኔ ግብፅንና ሱዳንን ይገዙ/ያስተዳድሩ ነበር፡፡ እና ያው አፄ ምንሊክ እንደምታውቁት ኢትዮጵያን ዘመናዊ (Modernize) ለማድረግ ፕሮግራም ነበራቸው (ባይጻፍም በህሊናቸው የነበረ ነገር ነው) አገሬን አሠለጥናለሁ የሚለው ማለት ነው፡፡አፄ ምንሊክ፣ ይሄን የመሰለ ነገር አለ ሲሏቸው፣ ወደ ሀገሬ ይምጣ ይሉ ስለ ነበር፣ ባንክንም በተመለከተ ከእንግሊዞች ጋር ተነጋግረው ያን ጊዜ Egypt, Cairo የእንግሊዞች ትልቅ ባንክ ነበረ፣ ከእዛ ሰዎች እንዲመጡ ተደርጎ አፄ ምንሊክ ከሾሟቸው እዚህ ካሉ ኢትዮጵያውያኖች ጋር አንድ ላይ ሆነው አቢሲንያ ባንክ የሚባል አቋቋሙ፡፡ አቢሲንያ የሚለው ቃል እንግዲህ፣ ድሮ ፈረንጆች የእኛን ሀገር አቢሲንያ ነበር የሚሉት፡፡ እኛ ያን ጊዜ ኢትዮጵያውያን ነን፣ ኢትዮጵያ ናት ሀገራችን ነበር የምንለው፡፡እነሱ ግን አቢሲንያ ብለው ይጠሩን ስለነበር፣ አቢሲንያ ባንክ ተብሎ ተቋቋመ፡፡እናም እነ አቶ ደበበ ይህን ባንክ ለማቋቋም ሲያስቡ ይሄ አቢሲንያ ተብሎ የተቋቋመው ባንክ ትዝ ይላቸውና ታሪካዊነቱንም በማሰብ በዚያ እንዲሰየም አደረጉ፡፡ በወቅቱ ይህን የባንኩን ስያሜ የተቃወሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምክንያታቸውም፣ ስሙ ለአሁኑ ጊዜ አይሆንም፣ በፖለቲካም፣ በነበረው የፖለቲካ አመራር ድንገት ላይወደድ ይችላል የሚል ነበር፡፡ በዚህም የሐሳብ መከፋፈል ስለተፈጠረ ካፒታል ያዋጡ ሰዎች (shareholders) ድምፅ እንዲሰጡበት ተደረገ፡፡ የድምፅ ቆጠራው ሲካሄድ 80ከ100 (80%) የሚሆኑት ይህን አቢሲንያ የሚለውን ስም ነው እኛ የምንቀበለው፣ እንዳውም በስሙ ምክንያት ነው ወደዚህ የመጣነው፣ ገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ስሙ ስቦን ነው፣ ይህ ስም በፍፁም መለወጥ የለበትም ብለው ተከራከሩ፡፡ 20ከ100 (20%) የሚሆኑት አልተስማሙም፣ እንደማስታውሰው ስሙን የተቃወሙት ከዚህ ወጥተው ሌላ ድርጀት (በመጀመሪያ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከዚያም ባንክ) አቋቋሙ፡፡ ስሙን በሚመለከት ያለው ታሪክ ይህ ነው ፡፡
ጥያቄ፡- በወቅቱ ከተቋቋሙ የግል ባንኮች አቢሲንያ ከሁሉም ቀድሞ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ያገኘ ነው ይባላል። አዋሽና ዳሽን ባንክ ወደ ሥራ ቀድመው በመግባታቸው አሁን ላይ አዋሽ የመጀመሪያው የግል ባንክ እያለ እያስተዋወቀ ይገኛል። እና ፈቃዱን ቀድሞ ያገኘው አቢሲንያ ባንክ ከነበረ ወደ ሥራ ሲገባ ለምን ተዘገየ?
መልስ፡- እንግዲህ ክርክር ነበር፣ ቅድም እንደተናገርኩት አንዱ ክርክር አቢሲንያ በሚለው ስም ላይ ነው፣ ሌላም የውስጥ አለመግባባቶች እንደነበሩ ትዝ ይለኛል። በርግጥ ይህ በተከሰተበት ወቅት እኔ በቦታው አልነበርኩም፣ ነገር ግን ጉዳዩ፣ መቼም በሀገራችን እንዲህ አይነት ችግር አለ፡፡ በርግጥ በሀገራችን ብቻም አይደለም ሁሉም ሀገር ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም እኛ የበለጠ ነገር እናከራለን። እንግዲህ ተባብሮ መሥራት ቀላል አይደለም፣ አንዳንዴ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል አስተሳሰብ እንዲሁም ግትርነት በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ አለ፣ ነበረ። እንግዲህ እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ተደማምረው ነው ቀድሞ ወደ ሥራ መግባቱን ያዘገዩት እንጂ፣ በወቅቱ ቀድሞ ካፒታል የሰበሰበው፣ በመጀመሪያ ፈቃድ ያገኘው፣ ሌላውንም ጉዳይ ቀድሞ ያከናወነው እውነት ነው አቢሲንያ ባንክ ነበር። ነገር ግን ይህን ያህል ስለቆየ ብዙ ተጐዳ ማለት አይቻልም። በርግጥ የመጀመሪያው ባንክ ነው ቢባል ለማርኬቲንግ ያመቻል፣ እናንተ የማርኬቲንግ ሰዎች ስለሆናችሁ ይህን ይሆናል የምታስቡት። ከማርኬቲንግ አንፃር ሲታይ ይህም ቢሆን ያን ያህል ብዙ ሰው የሚስብ ሆኖ ግን ለእኔ አይታየኝም።
ጥያቄ፡- አቢሲንያ ባንክን በሚመሩበት ወቅት የእርስዎ ፍላጐት ወይም ራዕይ የነበረው፣ በሠለጠኑት ሀገሮች (በተለይም በአሜሪካ በሚገኙት ባንኮች) ደረጃ የሚሰራ ባንክ ለማድረግ እንደነበር አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ። ይህ ምን ያህል ዕውነት ነው?
መልስ፡- እንግዲህ እንዲህ የሚሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል፣ እኔና፣ እኔ ብቻም አይደለሁም ከእኔ ጋር የነበሩ የሥራ በልደረቦቼም ሐሳብ የነበረው፣ መርህ የሚከተሉና ጥሩ ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎችን፣ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሠጥ፣ ሕዝብን የሚያገለግል፣ በምንም ነገር የማይታማ፣የሚመሠገን፣ ጥሩ ስም ያለው ባንክ፣ ፈረንጆች ሙያው የላቀ (Professional Excellence)፣ በሙያው የሚታወቅ፣ ባንክ ማለት ይሄ ነው እንዲባል ነበር የምንፈልገው፣ አሜሪካም እንግሊዝ ሀገርም ሳይ በዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ያንን ዓላማ ለመፈፀም በምንቀሳቀስበት ጊዜ በርግጥ ብዙ ችግር ነበር፣ ግን ዋናው አስተሳሰብ ይሄ ነው በዕውነቱ። ባንኩ በሙያ ጉድለት እንዳይነቀፍ፣ ይሄ አቢሲንያ ባንክ እንዳው ባንክ ነኝ ይላል እንጂ ስም ብቻ ነው፣ ሌላ ነገር የለውም እንዳይባል፣እንዲሁም ሰው የሚያምነው፣ በሚሠራው ሥራም ለሀገርም ለተበዳሪውም እጅግ ጠቃሚ የሆነ፣ ለወጣቶች የሥራ መስክ (ዕድል) የሚፈጥር፣ ወጣቶች ባንክ ውስጥ ገብተው በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለሙያዎች እንዲሆኑ፣ አቀጣጠሩም፣ የሠራተኞች ዕድገትም በሙያ ላይ የተመሠረተ ባንክ፣ ብቃት ያለው ጐበዝ የሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ ተወዳድሮ የሚገባበት፣ በጐሣ በምን በምን ሳይሆን፣ በሙያ ላይ የተመሰረተ አቀጣጠር፣በሙያ ላይ የተመሠረተ አሠራርን መሠረት ያደረገ ደንበኛ ባንክ እንዲሆን ነው። ይህን ይሆናል ሰዎች በአሜሪካን፣ በሰለጠነው ሀገር ደረጃ የሚሉት፡፡ እኔ ዕድል ገጥሞኝ ከሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያገኘሁትን ልምድ እንዲሁም ከሌላ ከማንበብና ከሰው ጋር በመነጋገር ያገኘኋቸውን የባንክ ሥራ ልምዶች ተጠቅሜ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ጥሩ ባንክ ለማቋቋም ነው፡፡ዕውነት ነው።
ጥያቄ፡- እኔ አቢሲንያ ባንክን ከተቀላቀልኩ ጀምሮ ባንኩ አንድ ነገር እንዳስብ አድርጐኛል እሱም ስለ ድርጅት ባሕል (organizational culture) ነው። በርግጥ ብዙ የሥራ ጊዜየን ከኮሌጅ በኋላ በሥራ ያሳለፍኩት በአንድ ድርጅት እሱም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፣ሆኖም ሁለቱን ባንኮች ብቻ ሳነፃፅር፣ በባሕል ደረጃ ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገር ያለ ቢሆንም በዛው መጠን አቢሲንያ ባንክ የተለየ የድርጅት ባሕል እንዳለው ለመረዳት ችያለሁ። ይህ ተፈጥሯዊ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ የድርጅት ባሕል የብዙ ነገሮች ድምር እንደ መሆኑ፣ አንዳንድ ነገሮች ሳይ፣ በዚህ ረገድ ከመሠረቱ ምን የተለየ ነገር ተሠርቶ ነበር እላለሁ። ለምሳሌ ደሞዝ ክፍያ በየ15 ቀን መሆኑ፣ የሠራተኛው የባለቤትነት ስሜት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ካለ፣ ከዚህ ጋርም ምናልባት በተጨማሪ ሊያያዝ የሚችለው፣ አሁን ድረስ ብዙ ባንኮች የሠራተኞች ዩኒፎርም የላቸውም ምናልባት እናት ባንክ እና ዘመን ባንክ ናቸው በዚህ ሊነሱ የሚችሉት። እናም እርሶ በወቅቱ ሠራተኛው የሚለብሰው ዩኒፎርም እንዲኖረው በማሰብ፣ ከአንድ የእንግሊዝ ኩባንያ ጋር እየተነጋገሩ እንደነበር ይነገራል። ስለዚህም ቢያጫውቱን።
መልስ፡- እኔ እንደ አጋጣሚ ሆኖ የሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት በስተቀር ደሞዝ በየ15 ቀን ነው የሚከፈለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ኒውዮርክ (UN, New York) ስቀጠር በየ15 ቀን ነበር:: ወደ ኢ.ሲ.ኤ. አዲሰ አበባ (ECA, Addis Ababa) ተዘዋውሬ ስመጣም እንዲሁ ነበር:: አፍሪካ ልማት ባንክም (Development Bank of Africa) በየ15 ቀን ነበር የሚከፈለው። ደሞዝ በየ15 ቀን መከፈሉ እኔ እንደሚገባኝ ጥሩ ነው። ወር መጨረሻ ሊደርስ ሲል ብዙ ሰው ይቸገራል፣ አንዳንድ ሰው ዕዳ ውስጥም ይገባል። እና ያን አይቼ ነው በየ15 ቀኑ እንዲከፈል ያደረግኩት። መጀመሪያ ላይ እንዳውም አንዳንድ የባንኩ ሠራተኞች የድሮውን ልምድ ላለመተው ሲሉ በየ15 ቀን መከፈሉን ተቃውመው ነበር። ይሄ እንግዲህ አንዱ ነው፣ ሌላው ደግሞ ሰው ሲቀጠር በችሎታው ነው መሆን ያለበት በሚል አቋም የተሠራው ነው። ትዝ እንደሚለኝ የመጀመሪያዎቹን ሠራተኞች ስንቀጥር፣ በጋዜጣ ክፍት የሥራ ቦታ አለን ብለን ማስታወቂያ አውጥተን ነው፡፡ በእዛ መሠረት ማከናወኑ ሁሉም የሚያደርገው ሳይታለም የተፈታ ነገር ነው፡፡ እኛ ምን አልን ጥሩ ጥሩ ወጣት በኢኮኖሚክስ፣ በአካውንቲንግ እንደዚህ የተመረቁ እንፈልጋለን፣ ስለዚህ ማስታወቂያው መውጣቱን ይውጣ ግን ጥራት፣ ችሎታ ያላቸውን ሠራተኞችን ለማግኘት፣ ወደ ዩኒቨርስቲ ደብዳቤ ልከን በኢኮኖሚክስ፣ በአካውንቲንግ በየዓመቱ መጨረሻ ከሚመረቁ ተማሪዎች መካከል በደረጃ የመጀመሪያዎቹ አምስቱን፣ በደረጃ ከ 1-5 የወጡትን የስም ዝርዝር ላኩልን፣ እንዲመዘገቡ ክፍት ቦታ እንዳለም ንገሩአቸው ብለን ፃፍንላቸው፡፡ስማቸው የተላከልንን የስም ዝርዝር ይዘን ማወዳደር ጀመርን፣ በማስታወቂያ መሠረት ያመለከቱትም ስማቸው ይላክልናል። ስናወዳድር ቀደም ሲል የያዝነውን ሊስት እያየን ከዩኒቨርስቲ የተላኩልን አምስቱ ውድድር ውስጥ መግባታቸውን ካረጋገጥን በኋላ ከእዛ ውስጥ ደግሞ በራሳችን መስፈርት ከአምስቱ ከ 1-3 የወጡትን እየመረጥን፣ በዚህ መንገድ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ልጆች እናገኝ ነበር፡፡ ሴት ይሁን ወንድ ክርስቲያን ይሁን ሙስሊም ከየት መጣ ሳንል ማለት ነው። እናም መጀመሪያ የተቀጠሩት በጣም ብቃት ያላቸው ልጆች ናቸው። ይሄ የቴለሮች፣ የፀሐፊዎችን፣ የጥበቃን እንዲሁም የፅዳት ሠራተኛንም ቅጥር ይጨምራል፡፡ ይህ ማለት የጥበቃና የፅዳት ሠራተኞች ዲፕሎማ አላቸው ለማለት ሳይሆን፤ የፅዳት ሠራተኛዋን ችሎታ ለማወቅ የት ቦታ ስትሠራ እንደነበር፣ ምን ምን አይነት ሥራ እንደሠራች እንዲሁም ተያያዥ ነገሮችን በማየት ነው፡፡ ሌላው ሴት ሆነች ወንድ ኢትዮጵያዊ እስከ ሆነች ድረስ በኢንተርቪው ጊዜ አይናችንን ጨፍነን ጥሩ መልስ የምትሰጥ/የሚሰጥ ብቁ አዕምሮ ያላት/ያለውን እንመርጣለን። እና በዚህ ዓይነት ነው ሠራተኛ የሚመረጠው። እንግዲህ ይሄ የሆነበት ምክንያት፣ የባለሙያ መስፈርት የሚከተል መሥሪያ ቤት ነው እንዲባልና፣ ደግሞም በዕውነቱ ሁሉም ደስ ብሎት በእኩል መንፈስ በጓደኝነት፣ በወዳጅነት እንዲሠራ ለማድረግ ነው። ይህ መሆኑ፣ እኔ ጠቅሟል እላለሁ። ሌላው ደግሞ፣ ሠራተኛው ከታች ጀምሮ ከፅዳት ሠራተኛ እስከ ላይ ድረስ ገንዘብ ላይኖረው ስለሚችል፣ አክሲዮን (share) ሊገዛ አይችልም ስለዚህ ገንዘብ እያበደርን አክሲዮን እንዲገዛ አድርገን፣ የብድሩን ክፍያ ከደሞዙ እየቀነስን ብንወስድ በሚል፣ ከታች እስከ ላይ ያለው ሠራተኛ አክሲዮን እንዲገዛ አደረግን። ይህ የሆነበትም ምክንያት፣ አንድ ሰሞን ገንዘብ ከፋይ/ተቀባዮች (Tellers) መቼም ወደ ባንክ ሲመጡ አይተውት የማያውቁትን ብዙ ገንዘብ handle ያደርጋሉ እና የሰው ልጅ ሁል ጊዜ ፈተና ውስጥ ነው ያለው፣ አንዳንዶቹ ትንሽ ገንዘብ እያጐደሉ ፈተና ላይ መውደቅ ጀመሩ፣ ያደግሞ በማግስቱ ማን እንዳጐደለ ስለሚታወቅ ወንጀል ነው የሰረቁትን ፖሊስ ይወስዳቸዋል፣ ያስራቸዋል፡፡ ይሄ ተደጋገመ እና እኔም የሥራ ጓደኞቼም አዘንን። እንዴ ይሄ ባንክ የተቋቋመው ጥሩ ጥሩ ተማሪዎችን ከዩኒቨርስቲ/ከኮሜርሻል ኮሌጅ እየቀጠረ ወህኒ ቤት ለመላክ አይደለም፣ ምን ይሻላል? እርግጥ ያጠፋ ይቀጣል ወንጀል ነው። ሌሎች እንዳያጠፉ እንደምሳሌ እንዲሆን ነው። ግን ፈተናው ሁልጊዜ አለ እና መቶ በመቶ የቅጣት መንገድ ነገሩን አያስቀረውም። ሌላ መንገድ መፈለግ አለብን፣ እስቲ ይህ ገንዘብ እንዳይፈታተናቸው አክሲዮን (share) እኮ ቢገዙ ያንን ገንዘብ አይነኩም አይሰርቁም ምክንያቱም የራሳቸውን ቤት/ባንክ ሀብት እንደሚሰርቁ ነው የሚታያቸው ብለን ሠራተኛው ብድር ተመቻችቶለት ሼር እንዲገዛ አደረግን።
የሠራተኛውን የሚከፈለውን ደሞዝ እናያለን፣ እንዲሁም ሠራተኛውንም በመጠየቅ፣ የሚቆጥበው 15-20 ሊሆን ይችላል ከእዛ ውስጥ 10 ልናበድረው እንችላለን ከዚህ የበለጠም ዕዳ ሊሸከም አይችልም እያልን፣ይህን ማድረግ ጀመርን። እና መጀመሪያ ጥቂት ሠራተኞች እያለም ብዙዎች እንደገዙ አስታወሳለሁ፡፡ እናም ይህ ሲሆን ከብሔራዊ ባንክ ሕግ ጥሳችኋል የሚል ነገር መጣ፡፡ እንግዲህ አንድ ሕግ አለ፣ እኔም ራሴ አውቀዋለሁ ከእኛ ጋርም የሚሠሩ የሕግ ባለሙያዎች የሚያውቁት ነገር ነው፡፡ በኃይለሥላሴ ዘመን የወጣ የፍትሀ ብሔር ሕግ ውስጥ ያለ ነው። ምን ይላል ‹‹አንድ ባንክ አክስዮን (share) ለመሸጥ ለሦስተኛ ወገን ብድር ሊሠጥ አይችልም›› ይላል፡፡ ለሦስተኛ ወገን ማለት ለውጭ ሰው ማለት ነው። እነዚህ ሠራተኞቻችን ሦስተኛ ወገን ናቸው? አይደሉም! አንደኛ ወገን የባንኩ አካል ናቸው፡፡ እንግዲህ እንደምታውቁት ባንክ ማለት መኪናው፣ ሕንፃው፣ ኮምፒውተሩ ምን አይደለም፡፡ ባንክ ማለት አንድ ኩባንያ ይፈጠራል፣ ያ ኩባንያ ሦስት አካላት አሉት የመጀመሪያው አካል ባለቤቶቹ ናቸው (Share holders) ሁለተኛው አካል የሥራ መሪዎች ሦስተኛው አካል ሠራተኞቹ ናቸው፣ ባንክ ማለት ይሄ ነው። ፈረንጆች Corporate Entity ይሉታል። አንደኛው ወገን ማለት ይሄ ነው፣ ሠራተኛው ሦስተኛ ወገን አይደለም፡፡ ስለዚህ ባንኩ ለሠራተኞቹ ብድር ሲያበድር ለሦስተኛ ወገን ነው ያበደርከው ተብሎ ሊከሰስ ሊወቀስ አይችልም፣ ሕጉን አልጣሰም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ይህን አድርጋችኋል ሲል አላደረግንም አልን፣ ከዛም ሕግ ስለጣሳችሁ ብር 10,000 ትቀጣላቹ ተባለ፣ ይህማ እንዴት ይሆናል?! ብሔራዊ ባንክ ሕግ ጥሳችኋል ካለ ጥሩ የሚሆነው የብሔራዊ ባንክ የሕግ ባለሙያዎች እና የአቢሲንያ ባንክ የሕግ ባለሙያዎች ተገናኝተው ሊፈቱት ይችሉ ይሆናል፡፡ ካልተፈታ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ከሳሽ አቢሲንያ ባንክ ተከሳሽ ሆኖ ፍርድ ቤት ነው የሚዳኘን፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከሳሽም፣ መቀጫ
ጣይም፣ ዳኛም ሊሆን አይችልም፡፡ አልን እንግዲህ ይሄ እንደምትገነዘቡት ብዙ ችግር ይፈጥራል፤ ብዙ ችግር ፈጠረ፣ እኛ አላጠፋንም ነው ያልነው። አንዳንዱን ነገር በቃል ነው የነገርኋቸው ይህ ተሰማ ብዙ ታሪክ ተከተለ፡፡ ከእዛ በኋላ አቢሲንያ ባንክ አይታዘዝም ተባለ፡፡ ደሞ የሄ አይታዘዝም የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ አዛዥ አይደለም ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን የሚቆጣጠርበት ሕግ አለ፡፡ በዚያ መሠረት ባንኮቹን ይቆጣጠራል ማለት Supervise ያደርጋል እንጂ ያዛል የሚል ነገር የለም፤ ይቆጣጠራል ነው፡፡ በእዛ መሰረት እኛ ከሕግ በላይ አይደለንም ያንን ሕግ እናውቃለን በእዛ እንገዛለን፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን Supervision ሕግ ጥሳችኋል ከሆነ የመምከር የመቅጣት እንዲህ ያለ መብት አላቸው እና በዚህ እንገዛለን። ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ አዛዥ ነው አቢሲንያ ባንክም አይታዘዝም አይባልም። ብሔራዊ ባንክ አዛዥ አይደለም ተቆጣጣሪ እንጂ፡፡ እንግዲህ ከዛ በፊት በኮሎኔል በመንግሥቱ ኃ/ማርያም አገዛዝ ዘመን (በደርግ) ጊዜ አንድ ወጥ የሆነ ነገር አለ ብሔራዊ ባንክ ከላይ አለ የግል ባንኮች የሉም፣ ሌሎች ንግድ ባንኮች በሙሉ በሱ ስር ናቸው፡፡ በእነ ኮሎኔል መንግሥቱ ጊዜ ብሔራዊ ባንክ አዛዥ ሌሎቹ ቅርንጫፎች ናቸው፡፡የተወረሱ nationalize የሆኑ ባንኮች አሉ Banko de Roma፣ አዲስ አበባ እነዚህ ሁሉ ቅርንጫፎች ናቸው ይታዘዛሉ፡፡ አሁን ሌላ ዘመን ነው፣ ሕግ ወጥቷል አዛዥ ታዛዥ የሚል ነገር አይደለም ያለው፡፡ በሕግ መሠረት ከላይ የሚቆጣጠር አለ፣ ያንን ተከትለው መሄድ ያለባቸው ባንኮች አሉ፣ ይሄው ነው። እንግዲህ ከጀርባ ብዙ ነገር አለ፡፡ እሱ ሰበብ እየሆነ ነው እንጂ በክፍት አዕምሮ፣ ፈረንጅ እንደሚለው ጥሩ ትርጉም አይደለም፣ እንደው በግልፅ እንደማለት ነው፣ ምንም ነገር አዕምሮአችን ውስጥ ሳይገባ ጉዳዩን ብቻ በመመልከት መነጋገር ብንችል ኖሮ፣ ምንም ችግር አልነበረው በቀላሉ ይፈታ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ሠራተኛውን ለአክሲዮን ግዢ የማበደር ነገር የመጣው እንደው ትልቅ ነገርን ለመከላከል ሳይሆን ትንሽ minor theft ለመከላከል፣ አንዳንድ ሠራተኞች (ገንዘብ እየቆነጠሩ የሚወስዱ ልጆችን) ቢሰርቁ ባንካቸውን ስለሚሆን አያደርጉትም በሚል ነው። የሠራ ይመስለኛል ካልተሳሳትኩ በስተቀር፣ ይህ ደግሞ በጣም ጥሩ የሆነ አንድ አይነት ስሜት በሠራተኛው ዘንድ ፈጠረ፣ እኛም የዚህ ባንክ ባለቤቶች ነን እኮ በሚል ሳይታዘዙ መሥራት፣ ለባንኩ መቆርቆር እንዲህ ያለ culture ፈጥሮ ነበር፡፡ እንግዲህ ቀጣይነት ይኖረዋል ብለን ነው ይሄን ያደረግነው፣ ቀጥሏል ወይስ በእዛው ጊዜ ቀርቷል የሚለውን ከእናንተ ነው አሁን የምሰማው፣ ምስክርነቱን እናንተ ትሰጣላችሁ። ከዩኒፎርም ጋር ተያይዞ የተነሳውን የመጨረሻውን ጉዳይ አላስታወስኩም፣ በርግጥ አላስታወስኩም ማለት አልሆነም ማለት አይደለም፣ ዕድሜዬም ገፍቶ ይሆናል።
ጥያቄ፡- ምስክርነት ላሉት እንግዲህ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሳይነሳ ቢታለፍ ትክክል የማይሆነው፣ እርሶ ያን ጊዜ ምናልባትም የብር 1,000 ዋጋ ያለው አክሲዮን እንዲገዙ ይሆናል በጊዜው ላሉ ሠራተኞች የፈቀዱላቸው፣ አሁን ላይ በጽሕፈት ሥራ ላይ ያልተሰማሩ ሠራተኞች እንኳን ከብር 100,000 በላይ ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ባለቤት ሆነዋል።
አቶ ተካልኝ፡- መቶ ሺህ ብር?!
ጠያቂ፡- አዎ በእውነት! የትርፍ ክፍያውን አክሲዮናቸውን ለማሳደግ እየተጠቀሙበት እና ገንዘብ ሲያገኙም እየጨመሩበት አሁን ላይ ከዚህ በላይ ዋጋ ያለው አክሲዮን እንዲኖራቸው ሆኗል፡፡ በተለያየ አጋጣሚም ዕድሜ ለአቶ ተካልኝ ገዳሙ እያሉ ሲያመሰግኑም ይደመጣሉ፡፡ ይህንን መመስከር ያቻላል፡፡
መልስ፡- መቼም በዚህ ብዙ አልከራከርም፣ እግዚሃር ይስጥልኝ! ይህን በመስማቴ ደስ ይለኛል፡፡
ጥያቄ፡- አቢሲንያ ባንክ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር የንግድ ግንኙነት ሲጀምር ሂደቱ ምን ይመስል እንደ ነበረ ትንሽ ቢያጫዉቱን፣ ሌላም የተለየ የንግድ ግንኙነት ታሪክ አለው የሚሉትም የባንካችን ደንበኛ ካለ እንዲሁ አያይዘው ቢነግሩን ?
መልስ፡ እንግዲህ አሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የሚሠሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ ለእነርሱ ደመወዝ የሚከፈለው፣ እነሱ ባላቸው መዋቅር ውስጥ የደሞዝ ክፍል አለ በዚያ ነው፣ እነርሱም እንግዲህ በ 15 ቀን ይሆናል የሚከፍሉት:: ነገር ግን፣ ሲያዩት ስራው እየበዛ ሄደና ምን አሉ፣ ገንዘብ ስንከፍል ገንዘብ እየቆጠርን፣ እያወጣን… ምን እያልን፣ ይህ ሁሉ የባንክ ሥራ ነው፣ ይህን ሥራ ባንክ ቢሠራልን ነው ጥሩ የሚሆነው ብለው የግል ባንኮችን ለማወዳደር አሰቡ፡፡ ያወዳደሩት እንደ መሰለኝ የግል ዘርፉን ትንሽም ለማደፋፈር፣ Encourage ለማድረግ ነው። ከተቋቋሙት የግል ባንኮች መካከል አንደኛውን በጥራትና እንደዚህ ባለ ነገር አወዳድረን መርጠን ቅርንጫፍ ተከፍቶ፣ ቅርንጫፉ ይህን እንዲሠራልን እንፈልጋለን በሚል ማስታወቂያ ያወጣሉ ። ይህን ማስታወቂያ ስመለከት፣ ይህ ትልቅ ዕድል ነው በማለት ሁለት ሶስት የሥራ ጓደኞቼን ጠርቼ ተነጋገርን፣ ይህ የመጀመሪያ መታወቂያችን ይሆናል ቀልጠፍ ባለ ሁኔታ ደግሞም ይህን አሟሉ ያሉትን ሁሉ አሟልተን በዚህ ቀን ቢዘገይ በዚህ ቀን እናቅርብ አልኳቸው፡፡ ተወዳዳሪዎቻችን በመጨረሻው ማስረከቢያ ቀን offer ሊያስገቡ ይችላሉ። እኛ ግን አንድ አራት አምስት ቀን ቀደም ብለን እናስገባ አልኳቸው፣ ቶሎ ሰርተን የሚታረም ነገር አስተካክለን ከተባለው ቀን ከሳምንት በፊት አስገባን። ትዝ እንደሚለኝ፣ የተሰጠን ጊዜ ቀኑም ደረሰ ከዚያም በኋላ ጥቂት ቀን አራት አምስት ቀን ይሆናል፣ ከኢምባሲው ስልክ ይደወልና አሸንፋችኋል ተባልን፣ ደስ አለን። አሸንፋችኋል ያለው ሰውዬ፣ እኔ የዚህ ክፍል ሰራተኛ ነኝ፣ መጥቼ አንተንና የስራ ጏደኞችህን በግንባር መተዋወቅ እፈልጋለሁ አለ፣ መጣ ተገናኘን። በጣም በፍጥነት ነው የናንተ offer የደረሰን። ሁለተኛ ደግሞ ጥራት ያለው ሥራ ነው። ደስ ብሎናል አለኝ። አንድ ሚስጥርም ልንገርህ አለኝ፣ የማስረከቢያ ወቅቱም ካለፈ በኋላ የላኩ ባንኮች ነበሩ። ደግሞ ከመላካቸውም በፊት በሥራው ላይ አንድ አንድ ጥያቄ አለን ብለው ነበር። እኛም እንዴ! ጊዜው እኮ አልፏል አልናቸው፣ እንዴት ያልፋል?! አሉ። ግዜው ማብቃቱም ብቻ ሳይሆን እኛ አሸናፊም መርጠናል አልናቸው። ማንን መረጣችሁ ብለውም ሲጠይቁ የእናንተን ስም ነገርናቸው። እንግዲህ ጥሩ ነው በርቱ ብለውን ሄዱ። ይህ ለእኛም ስም ጥሩ ነበር፡፡ አሁን እንደምሰማው ስራው ተስፋፍቶ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳለ ነው፡፡ እንግዲህ ቅድም እንዳልኩት ሁል ጊዜ ሥራን በጥራት መሥራት ደግሞም Competitive መሆን፣ ተወዳዳሪነት በባንክ ዓለም በጣም አስፈላጊ ነው። እንደምታውቁት 1ኛ ወይም መሪ ሆኖ መገኘት በጣም ደስ ይላል። በተለይ ለሠራተኛውም ጥሩ ነው። ጠዋት ሲመጣ ደስ ብሎት ነው የሚመጣው። እንደዚህ ዓይነት ድርጅት ውስጥ በመሥራቱ ክብር ይሰማዋል። ይህንን ስሜት ባንክ ውስጥ መፍጠር ያስፈልጋል። ሌላው ይህን Interview ከመጀመራችን በፊት ያወራነው አንድ ጉዳይ አለ። እዚህ ጋር ባነሳው ጥሩ ነው፣ እሱም ከUSAID ጋር ያደረግነው ስምምነት ነው፡፡ እኛ ቀደም ሲል አቢሲንያ ባንክ በገጠር የሚገኙትን ገበሬዎች እንዴት ሊረዳ ይችላል:: ያው እኛ ከተማ ውስጥ ነው ያለነው፣ በምን መልኩ እነሱ ጋር እንድረስ፣ ብድር እንዳንሰጥ ገበሬዎች ዋስትና የላቸውም፡፡ ድሮ በአፄ ሐይለ ሥላሴ ጊዜ ገበሬዎች ወይም ባለርስቶች ብድር ሲፈልጉ፣ መሬት ይሸጣል ይለወጣል እሱን አስይዘው ይበደራሉ። በዚያ መሠረት ሥራቸውን ያካሂዳሉ። እኔ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ከሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያን ጊዜ አንዱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደመሆኑ፣ እዛ ሳለሁ ብዙ የእርሻ ብድሮችን እንሰጥ ነበር። ቅድም እንዳልኳችሁ ርስታቸውን እያስያዙ ነው ብድር የሚወስዱት፡፡ አሁን ርስት የለ ምን የለ ምን ይሻላል። ይሄ ባንክ ደግሞ ስራውን ማስፋፋትም አለበት። ሥራውን ሲያሳድግ ደግሞ ወደ ገበሬዎችም መሄድ አለበት፡፡ በዕውነት! ተጨንቀን ነበር፡፡ “በአሁኑ ጊዜ ዋስትና የለም ብለን እንነጋገራለን፣ ነገር ግን ከመጨነቅ ከመጠበብ ውጪ ምንም ያደረግነው ነገር የለም ” እያልን ነበር። እዚህ ደረጃ ላይ እንዳለን አንድ ቀን ከUSAID (የታወቀ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ነው)፣ አንድ ሰው ይመጣና፣ በአሁኑ ጊዜ ገበሬው ከእናንተ ሊበደር አይችልም፣ ምክንያቱም በዋስትና መልክ የሚያቀርበው ሀብት የለውም። እኛ በዚህ ጉዳይ እናንተ ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ ለገበሬዎች ማበደር ከፈለጋችሁ ሲል፣ እኔ ትንሽ ሳቅ አልኩ፣ ይሄ ሰውዬ ጠንቋይ ቀልቧል ወይስ ምንድን ነው? ምክኒያቱም ያንን ነበር በወቅቱ የምናስበው፣ ፍቃደኞች ከሆናችሁ 50% የገንዘብ (CASH) ዋስትና፣ ማለትም፣ ለምሳሌ ለአንድ ሰው ብር 10,000 ብታበድሩ፣ የ ብር 5 000 የገንዘብ ዋስትና በባንካችሁ እናስቀምጣለን፣ ከፈለጋችሁ በዶላር ሊሆን ይችላል ካልሆነም በብር። ለእያንዳንዱ ተበዳሪ ማለት ነው። እኔ መቼም በዕውነቱ ጆሮዬ የሚሰማው ትክክለኛ ነገር ነው ወይስ ሌላ አልኩኝ፣ ምክንያቱም ቅድም እንደነገርኳችሁ በዚህ ጉዳይ ነበር ስንጠበብና ስንጨነቅ የነበረው፡፡ ምን አልኩ በልቤ 50 በ 100 ከተሸፈነልንማ በ50% ላልጨነቅ እችላለሁ፡፡ ምክንያቱም ከእዛ በላይ የሚከስር ያለ አይመስለኝም፡፡ ቢከስር 10 በ 100 ወይም 20 በ100 ነው፡፡ በሙሉ ከከሰረ ደግሞ እንግዲህ በReserve እይዛለሁ ብዬ፣ ጥሩ ነው እንቀበላለን አልኩት፣ ከዛም ስምምነቱን ተፈራረምን። አሁን ምን አይነት ደረጃ እንዳለ አላውቅም። አሁንም ያለ ይመስለኛል ። ይሄን ደግሞ የፈረንሳይ ኢምባሲ ሰዎች ሰምተው ይመጣሉ። የUSAIDን ስምምነት አንስተን፣ አዎ እንዲህ ተደርጏል አልናቸው። እኛ ደግሞ፣ ከተማ ውስጥ ላሉ ዋስትና ማቅረብ ለማይችሉ፣ ትንንሽ Cottage Industry ብድር መስጠት እንፈልጋለን አሉ። ተመሳሳይ ውል ብንፈራረምም አሉ፡፡ ደስ ይለኛል ጥሩ ነው አልኩ፡፡ ነገር ግን ይሄኛው ወቅቱ እኔ የምሄድበት በመሆኑ አልተጠናቀቀም፣ እንዲህ ያለ ነገር ተጀምሮ ነበር ለማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን አሁንም ላይ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ጥያቄ፡ ወደ ባንክ ዘርፍ እንመለስና፣ በሀገራችን የሚታየው በብሔር፣ በሃይማኖት ላይ መሠረት ያደረገው የባንክ አመሰራረትና አካሄድ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ይበጃል ይላሉ? መልስ፡ ይሄን መቼም መገመት ትችላላችሁ፡፡ ያኔ ስንጀምር የተናገሩኩትን ላጫውታችሁ፣ በወቅቱ ጥቂት ባንኮች ነበሩ እና ከጀርመን ከእንግሊዝ ሀገር እንዲሁም ከአሜሪካ Correspondent Banking Relationship ለመፍጠር፣ ማለትም Export/Import ረገድ እኛን Correspondent Bank ለማድረግና ከእኛ ጋር ለመሥራት እንደ Citi Bank ያሉ ባንኮች እኛ ጋር ይመጡ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከDeutsche Bank አንድ ሶስት አራት ልዑካኖች ይመጣሉ፣ እና መጥተው ስንነጋገር ምን አሉ፣ እናንተ ሀገር አንድ አዲስ አሠራር አለ በእኛ አስተያየት ጥሩ ነው፡፡ እናም በዚህ ረገድ አንድ ጥያቄ ልንጠይቅህ እንፈልጋለን አሉኝ፡፡ ጥሩ ነው ያላችሁት ምኑን ነው አልኳቸው፡፡ እንደሰማነው እያንዳንዱ ባንክ የሚመሠረተው በብሔር ነው፣ እያንዳንዱም ብሔር የራሱ ባንክ አለው እንደ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የአንተ ባንክ በየትኛው ብሔር ላይ ነው የተመሠረተው ይሉኛል፡፡ የእኛ ባንክ የተመሠረተው ኢትዮጵያ የሚባል ብሔር አለ በዚያ ላይ ነው አልኩት፣ ይሄን ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ አሁን እናንተ እንደምትስቁት ሳቅ አለ፡፡ እሱማ ኢትዮጵያኮ ኢትዮጵያ ነች አለ፡፡ ቀደም ብሎ ጥሩ ነው ያለበትን ሲያስረዳኝም፣ ከውጭ ሀገር የመጣን ሰዎች ጥሩ ነው ያልንበት አሠራር ምክንያት፣ አንድ ባንክ ሲቋቋም ብዙ ችግር ያጋጥመዋል፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ ለማግኘት፣ ተበዳሪ ለማምጣት፣ ደንበኛ ለመሳብ ይቸገራል፡፡ በጎሣ ከተመሠረተ ግን የዚያ የባንኩ ጎሣ ዝም ብሎ አይኑን ጨፍኖ ይመጣና ገንዘብ ያስቀምጣል፣ ብድርም ይበደራል፣ ባንኩን ይደግፈዋል፡፡ ስለዚህ በተወሰነ ደራጃም ቢሆን በጣም ጥሩ Minimum Client Base ይኖረዋል፣ ያ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሩ ነው፣ ብሎኝ ነበር፡፡ መልሶም ቅድም እኮ ትንሽም ቢሆን ጥሩ Client Base አለው ብለኸኝ ነበር ሲለኝ፤ አዎ የእኛ Client Base ኢትዮጵያ የሚባለው Ethinic ነው፣ እሱ ደግሞ ሠፊ Base ነው አልኩት፡፡ አሁንም ይስቃል፣ አንተ ክርክር ትወዳለህ አለኝ፡፡ አይ ይሄ ክርክር መውደድ ሳይሆን ከኢኮኖሚ አንጻር ስታዩት ሠፋ ቢል ነው የሚሻለው፣ ደግሞም መንፈሱ እንደዛ ነው፡፡ ከአማራ ከኦሮሞ ከትግሬ ከሁሉ ጋር ወንድማማቾች ነን፣ እናም እንደዚያ ቢታሰብ ነው ጥሩ የሚሆነው፡፡ ግን ደግሞ አሁን ላይ ለምን እንደዚህ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ አንዱ ጎሣ በዚህ መልኩ ሲያቋቁም ሌላው እኔስ ይላል፣ Logical የሆነ ነገር ነው፡፡ እኔ ግን ህሊናዬ መንፈሴም አይቀበለውም፡፡ በርግጥ፣ እኔ ተቀበልኩ አልተቀበልኩ ለሌላው ቁም ነገር አይደለም፣ ነገር ግን እኔ የምሰጣችሁ የግሌን አስተያየት ነው፡፡ በሌላ ሀገር እንደዚህ ያለ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እኔ ግን በኢትዮጵያ ደረጃ፣ በኢኮኖሚ እይታ ጥሩ የሚመስለኝ ገበያው አንድ ቢሆን ነው፡፡ በፖለቲካ ስሜት ልዩ ነን ከሚለው መልዕክት ውጪ ገበያው Fragmented ሲሆን ጥሩ አይደለም፡፡ ይሄን የሚሠሙ በAlternative ጎሣ ወይም በሃይማኖት የተመሠረተ ባንክ የሚያቋቁሙ ሰዎች፣ አቶ ተካልኝ እንደው ትክክል አይደለም ሊሉኝ ይችላሉ፣ ካሉኝ ደግሞ ያ የእነሱ አመለካከትና ሐሳብ ነው፡፡ ለአንዱ ወገን ሳይሆን ለሁላችንም ፣ ለዚች ሀገር ጥሩ የሚሆነው አንድ ላይ ሆኖ መሥራት ነው፡፡ ፈረንጆቹ Economy of Scale የሚሉትም ከዚህ ጋር ይገናኛል፡፡
ጥያቄ፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ Stock Exchange ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይሄ የባንክ ዘርፉን ወይም ኢኮኖሚውን በምን መልኩ ወይም ደረጃ ይቀይረዋል ይላሉ?
መልስ፡ ኦ! ይሄ መቋቋሙ ጥሩ ነው፡፡ በተፋጠነ አኳኋን ለሀገር ልማትን ለማካሄድ ለሚፈልግ መንግሥት ማንኛውንም መንገድ፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥረውን፣ ኢንቨስትመንት የሚያስፋፋውን፣ ልማት የሚያመጣውን ማንኛውንም ነገር እያየ መከታተልና መጠቀም አለበት፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት Don’t leave any stone unturned! ማንኛውንም ድንጋይ መፈንቀል ነው፣ የተቀመጠውን ድንጋይ፣ ከሥሩ አንድ ነገር እንዳለ ለማየት ማለት ነው፡፡ በርግጥ Stock Exchange ኢትዮጵያ ወስጥ ቢቋቋም በአንድ ጊዜ ኢኮኖሚውን እላይ አያደርሰውም፡፡ ብዙ ነገሮች፣ ፕሮግራሞች ሲጀመሩ እና አንድ ላይ ተደምረው ነው ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅሱት፡፡ እንግዲህ Stock Exchangeን በተመለከተ አንድ ነገር ልንገራችሁ፡፡ እዚህ አቢሲንያ ባንክ እያለሁ፣ በዚያን ጊዜ፣ በዚህ ረገድ (Stock Exchangeን በተመለከተ) ሰው የሚያየው አንድ እርምጃ ወስደን፣ አንድ ነገር እናድርግ ብለን ተነሳን፡፡ እና ከዚህ በመነሳት ከሌሎች ባንኮች ጋርም በዚህ ጉዳይ ተነጋግሬአለሁ፣ እናም አንድ በዚህ ዙሪያ ጥናት እንዲያጠናልን የWorld Bank ቅርንጫፍ የሆነ IFC, International Finance Corporation የሚባል ድርጅት አለ፣ የግል ሴክተሩን የሚደግፍ ፣ በግል ሴክተሩ ውስጥ Invest የሚያደርግ ድርጅት ነው፡፡ ያኔ እነሱን የሚወክል አንድ ሠራተኛ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ቀደም ሲል አፍሪካ ልማት ባንክ በነበርኩበት ወቅት አብረን እንሠራ ስለነበር እንተዋወቃለን፡፡ አንድ ቀን ጠርቼ አነጋገርኩት፡፡ የነገርኩት ምንድን ነው፣ በአፄ ሐይለሥላሴ ጊዜ ወደ መጨረሻው አካባቢ እንዲህ ያለ ነገር ተጀምሮ ነበር፣ Stock Exchange ለመጀመር የመጀመሪያው እርምጃ ተወስዶ ነበር፡፡ እርሱም Share Dealing Group የሚባል የብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩ አቶ ምናሴ ለማ የሚባሉ ሊቀመንበር የሆኑበት እና ሌሎች የመንግስት ድርጅቶች Share የገዙበት ተቋቁሞ ነበር፡፡ እኔ ያኔ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሥራ አስኪያጅ ነበርኩ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እዛ ግሩፕ ውስጥ ሼር ነበረው፡፡ ይሄን ግሩፕ የፈጠረው በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት የኢትዮጵያ መንግስት ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴርም Stock Exchange ለማቋቋም ሼሩን ለመንግስት ድርጅቶች አከፋፈለ፡፡ ነገር ግን በግል ዘርፉ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሰዎች ይህን ብዙም የሚገነዘቡ አልነበሩም፡፡ አቶ ምናሴ ይህን የማቋቋምና የመምራት ኃላፊነት ተሠጥቷቸው ነበር፡፡ እናም ብሔራዊ ባንክ ትልቁን ሼር እንዲገዛ ተደረገ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እንደ ሲሚንቶ ያሉ አንዳንድ የመንግስት ኮርፖሬሽኖች አንድ ላይ ሆነው ያ ድርጅት/ግሩፕ ተፈጠረ፡፡ ያ ግሩፕ ከተፈጠረ በኋላ ሼር Deal ማድረግ ጀመረ፡፡ ለምሳሌ እኔ ትዝ ይለኛል ሰው መቼም የራሱን ነው የሚያስታውሰው፡፡ በወቅቱ አንድ መድሃኒት ፋብሪካ እንደ ሼር ኩባንያ ተቋቋመ፡፡ የመንግስት ኩባንያ ነው ነገር ግን ሼሩ ለህዝብ ተሸጠ፡፡ የኩባንያው አብዛኛው ሼር በመንግስት የተያዘ ነው፡፡ እኔ ወጣት ስለነበርኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ሼር የሚሸጥ ካለማ ጥሩ ነው ብዬ ሄጄ ሼሩን ገዛሁ፡፡ ከዛም የእዛ መድሃኒት ፋብሪካ ሼር ከቀን ቀን እየቀነሰ መጣ፡፡ ይህንንም በወቅቱ State Bank of Ethiopia ይባል በነበረው ፣ ቆይቶም የአሁኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ብሔራዎ ባንክ ተብሎ ለሁለት እንደ አዲስ በተቋቋመው መከታተል ይቻል ነበር፡፡ ያን ጊዜ አቶ ምናሴ ሁለቱንም መሥሪያ ቤት ያስተዳድሩ ነበር፡፡ እናም የመድሃኒት ፋብሪካው ሼር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መስኮት ላይ ከውጪ በሚታይ መልኩ መስታወት ላይ ይለጠፍ ነበር፡፡ እኔ በሳምንት ሁለት ሶስቴ እየሄድኩ ስመለከትና ስከታተል የገዛሁት ሼር ዋጋው ዝቅ እያለ ይሄዳል፡፡ እረ! መሸጥ አለብኝ አልኩ፡፡ የት ነው ግን የምሸጠው? እያልኩ እያለ አንድ ቀን Share Dealing Group ውስጥ ጉዳዩን በዚህ መልክ አነሳሁት፣ ይሄ የመንግስት ኮርፖሬሽን ነው ሼር ይሸጣል፡፡ ሼሩ እየወደቀ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የእኔን ሼር መሸጥ እፈልጋለሁ አልኩኝ፡፡ አቶ ምናሴ አምጣው እኔ እገዛሃለው አሉ፡፡ ለእሳቸው ወዲያው ሸጥኩት፡፡ እንግዲህ እሳቸው ምሳሌ ለመስጠትና ለማበረታታት ነው ይህን ያደረጉት፡፡ ያወጣሁት ዋናው ሳይነካብኝ ትንሽ ከስሬ ሸጥኩት፡፡ የዚህ ሐሳብ ዓላማው ምን ነበር፣ የኋላ ኋላ የተሟላ በደንብ በሕግ የተቋቋመ Stock Exchange ለመመሥረት ነበር፡፡ እና ለዚህ ለፈረንጅ ለIFC ሰው፣ አንድ ጥናት ልታስጠኑልን ትችላላችሁ ወይ አልኩት፡፡ እረ! በደስታ እንጂ አለ፡፡ ሥራችን ነው፣ እኛ የግል ዘርፉን ማበረታታት ነው የምንፈልገው፡፡ ያንን እናደርጋለን፣ እናንተ ብዙ ገንዘብ አታወጡም፡፡ ጥናቱ 50000 ዶላር ያወጣ ይሆናል አለ፡፡ ግን ትንሽ መንፈሳችሁን ለመግለጽ ያህል ትንሽ ገንዘብ አዋጡ አለ፡፡ የእኛ ባንክ የተወሰነ ገንዘብ አዋጣ ሌሎች ባንኮች ትንሽ ተጠራጠሩ፡፡ ጥናቱም ተሠርቶ መጣ፡፡ ጥናቱም፣ Stock Exchange ከመቋቋሙ በፊት መንግሥት ሕግ ማውጣት አለበት፡፡ ማን Regulate ያድርገው፣ እንዴት ይሥራ የመሳሰሉ ዝርዝር ሁኔታዎችን በሚመለከት መንግሥት ሕግ ማውጣት ይኖርበታል፡፡ ስለዚህም ጉዳዩን ለመንግሥት አቅርቡ፣ ልማቱን ሊደግፍ የሚችል አዲስ ድርጅት ሊሆን ይችላል መጀመሪያ የሚቋቋመው፣ የሚል ነገር ይዞ መጣ ፡፡ ያን ጊዜ ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ እንደሚሻል መከሩን፣ ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መለስ ነበረ፣ ጥያቄውም በአቶ ንዋይ በኩል ቀረበለት፡፡ የማስታውሰው የተሰጠው መልስ በእንግሊዝኛ ነው፣ የደረሰን በቃል ነው፣ ይሄ የእኛ Priority አይደለም የሚል ነበረ፡፡ ይሄ ለእኛ አንገብጋቢ ጥያቄ አይደለም እንደ ማለት ነው፡፡ በዚያ መልኩ ቀረ፡፡ አሁን በአዲስ መንፈስ የሚጀመር ከሆነ የሚደገፍ ነው፡፡ እንዳልኳችሁ፣ ያልተጠበቀ ኢኮኖሚውን ከዚህ አንስቶ ሠማይ የሚያስነካው አይደለም፡፡ ልማት በዚህ መልኩ አይደለም የሚመጣው፡ ብዙ ልዩ ልዩ ኢንቨስትመንቶች ሲደረጉና ሲደጋገፉ ነው፡፡ አንድ ነገር ብቻውን ይህን ኢኮኖሚ ሊያስፈነጥረው አይችልም፡፡ Stock Exchange መጀመሩ ጥሩ ነገር ነው፡፡ እና ለምሳሌ ፣ በአሁኑ ጊዜ የባንክ ሼር የት ነው የሚሸጠው? እኔ ትዝ ይለኛል በአቢሲንያ ባንክ አንድ ትንሽ ሼር ሽያጭ ክፍል ነበረች፡፡ ሌሎችም ባንኮች እንዲህ ያደርጉ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጥሩ የሚሆነው፣ ለባንኮችም ለማንኛውም ሼር ላለው ድርጅት ሼሩን የሚገበያይበት አንድ ገበያ ያስፈልገዋል፡፡ እንግዲህ Stock Exchange ማለት እሱ ነው፡፡ እናም የባንኮች፣ የድርጅቶች አካሄድ እየታየ ሼር ይሸጣል ይለወጣል፡፡ መጀመሪያ ላይ ቅድም ያልኳችሁ የሼር ሽያጭ ክፍል አቢሲንያ ባንክ ውስጥ ከመቋቋሙ በፊት አንድ ሴትዮ ቢሮ ይመጣሉ ፣ የ500 ብር አንድ 20 ሼር ይመስለኛል ገዝተው ነበር፡፡ እናም በገዙ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ቢሮ መጥተው ፀሐፊዬ አንድ ሴትዮ ትፈልግሃለች፣ ብላኝ ይገቡና፣ የእኔ ልጅ ሰው መክሮኝ ሼር ገዝቼ ነበር፣ አሁን ገንዘብ ተቸገርኩ ምን ይሻለኛል አሉ፡፡ በጣም አዘኑ ተጨነቁ፣ 500 ብር ነው? እኔ እገዛዎታለሁ፣ ችግር የለውም ብዬ 500 ብር ሠጠኋቸው፡፡ መርቀው ደስ ብሎአቸው ሄዱ፡፡ አሁን ያን ጊዜ ሼር የሚሸጥበት ቦታ ቢኖር ኖሮ በትርፍ ሁሉ ሊሸጡት ይችሉና ትርፍ ያገኙበት ነበር፡፡ እኔ ያኔ 500 ስላሉ 500 ብር ሰጥቻቸው ሼር ገዛሁ ማለት ነው፡፡ በኋላ ደግሞ ይሄ ነገር ሲደጋገም ስሟ አሁን ላይ ጠፋኝ (ወ/ሮ ማዕረገሕይወት ውድነህ) በእዛ ወቅት ሒሳብ ክፍል አንድ ልጅ ነበረች፣ ሼር መግዛትም መሸጥም የሚፈልጉ ሰዎችን ትመዘግብና እያገናኘቻቸው ይሠራ ነበር፡፡ አሁን እንደምትሉት ይሄ በሀገር ደረጃ በአዲስ መንፈስ የሚመጣ ከሆነ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ጥያቄ፡ አሁን ላይ በባንክ ዘርፍ ኢንቨስተሮችም ባንኮችም ብድር ከውጭ ማገኘት እስከሚችሉ ድረስ አዳዲስ ሕጎችና አሠራሮች እየጸደቁ ይገኛሉ፡፡ እርሶ እንደው ከሚታዮት፣ እንዲህም ሊደረግ ይችላል የሚሉት ያልተኬደበት መንገድ ካለ? መልስ፡ በጣም ጥሩ ደስ ይላል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያለውን ነገር International Finance Corporation (IFC) አለ፡፡ እዚህ አሁን ሰው ይኑራቸው አይኑራቸው አላውቅም፡፡ IFC የግሉን ዘርፍ የሚደግፍ World Bank የአቋቋመው ትልቅ ድርጅት ነው፡፡ እዚህ ሰው ባይኖራቸውም ከዓለም ባንክ ወኪል ጋር ተነጋግሮ መተባበር ነው፡፡ እንግዲህ IFC በዓለም ባንክ ደረጃ ያለ ነው፡፡ ሌሎች እንደ እንግሊዝ ያሉ ሀገራት፣ European Union፣ የብዙ ሀገራት ድርጅቶች እና እያንዳንዱ ሀገር ደግሞ የልማት ፕሮግራም አለው፣ Bilateral ይሉታል ፈረንጆች፣ ሀገር ለሀገር አይነት ነው፣ ሀገራት ደግሞ ተሰብስበው የሚያቋቁሟቸው ቅድም እንደአልኩት ዓይነት ድርጅቶች አሉ፣ ብቻ በሁሉም መንገድ ዕድገት የሚያመጣን ነገር መፈለግ ነው፡፡ የግል ዘርፉ እንዴት ሊያድግ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ መንግስትም ያስባል፣ የሚያደርግም ይመስለኛል፡፡ ይህ እንግዲህ በግል ዘርፉ ውስጥ ነው በበለጠ ሁኔታ ሊሠራና ሊንቀሳቀስ የሚችለው፡፡
ጥያቄ፡ አሁን ላይ ያለውን አቢሲንያ ባንክ እንዴት አገኙት?
መልስ፡ እነ አቶ በቃሉን አግኝቼ አነጋግሬአቸው ነበር፣ በዕውነቱ! አያያዛቸው ጥሩ ነው፡፡ አቶ በቃሉ የታወቀ ፕሮፌሽናል ባንከር ነው፡፡ ጥሩ ስም ያለው ነው፡፡ ከየአቅጣጫው የምሰማው ነገር ነው፡፡ እኔም ሳነጋግረው የምወስደው Impression ይሄንኑ ነው፡፡ ስለዚህ አቢሲንያ ባንክን በተስፋ ነው የማየው፡፡ እሱና ከእሱ ጋር የሚሠሩት ትጉህ፣ ጠንካራ እንዲሁም ባለሙያ ሠራተኞች ናቸው፡፡ እንደ አጋጣሚ አንዳንዶቹንም በግንባር አግኝቼአቸዋለሁ፡፡ ከከተማም በወጣሁበት ወቅት ንቁ ንቁ ሠራተኞች እንዳሉ አይቻለሁ፡፡ ይህንን ሳይ ደስ ነው የሚለኝ፡፡ እናም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብዙ ብዙ ጥሩ ነገሮች የምናይ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የእኔንም ተስፋና ድጋፍ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ጥያቄ፡ አሁን ላይ ምን እየሠሩ እንዳሉ ቢያጫውቱን? መልስ፡ በመሠረቱ አሁን ላይ ጡረታ ላይ ነኝ፡፡ ግን መቶ በመቶ ጡረታ ላይ አይደለሁም፡፡ ከሌሎች ጋር ሆኜ አንድ ፕሮጀክት ላይ እየሠራሁ ነው፡፡ የዛሬ አስራ አንድ አመት አሜሪካን ሀገር ስሄድ ለመኖር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ረጅም ነው፡፡ ባለቤቴና ልጆቼ Philadelphia ስለነበሩ ወደ እዛ ነበር ቀጥታ ያቀናሁት፡፡ እዛ የሚገኙ ትልልቅ ኩባንያ ውስጥ ጥሩ ሥራ የሚሠሩ ትልልቅ Position ያላቸው በዩኒቨርስቲ ውስጥም የሚያስተምሩ በንግድም ያሉ ኢትዮጵያውያን በዕድር ሰበብ ተገናኝተን አንድ ጥያቄ ጠየቁኝ፡፡ ጥያቄው ምንድን ነው? እዚህ ለምንሠራው ኢትዮጵያውያን ብዙ ንግድ ቤቶች ሬስቶራንቶች፣ ግሮሠሪ፣ አገልግሎት የሚሠጡ የግል ክሊኒኮች፣ ጠበቆች፣ ታክሲ ነጂዎች፣ ሪል አስቴት በመሸጥ በመለወጥ የተሠማሩ ብዙ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከጀርባቸው ሆኖ የሚያደፋፍራቸው፣ ብድር ሲፈልጉ የሚሠጣቸው፣ አንዳንድ የኢንቨስትመንት Opportunity የሚጠቁማቸው ባንክ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እናም ይሄን ለማቋቋም፣ ቀደም ሲል ከአፍሪካ ልማት ባንክ ስራዬን አብቅቼ ወደ ሀገሬ ለመመለስ ሳስብ፣ ልጆቼን ትምህርት ቤት ለማስገባት ከባለቤቴ ጋር በቀጥታ ኢትዮጵያ ሳይሆን አሜሪካን ሄጄ ነበር፡፡ እዛ ጥቂት ጊዜ ቆይተን ልጆቻችንን ትምህርት ቤት አስገብተን፣ ወደ እዚህ ልንመለስ ስንል፣ እንግዲህ ይሄ የዛሬ 26 ዓመት ገደማ ነው፣ እንደዚህ ያለ ግሩፕ ስሜን አንድ ሰው ሰጥቶአቸዋል መሰለኝ፣ ይደውሉና ባንክ ልናቋቁም ነው ሳይሆን፣ የንግድ ምክር ቤት ልናቋቁም ነው፣ ይሄ የንግድ ምክር ቤት ሌሎች ነገሮችን ወደ ፊት ሊያቋቁም ይችላል ነበር በወቅቱ ያሉኝ፡፡ እኔማ ጠቅልዬ ወደ ሀገሬ መግባቴ ነው፣ እኔ አልጠቅማችሁም፣ እናንተ እንደዚህ ያለ ነገር እንሠራለን የምትሉት እዚህ ሀገር ነው፣ ብዬ ተመልሼ ነበር፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች ይህን ነገር ሲያነሱብኝ ያ ሥራ ነው እስከ ዛሬ ድረስ ሲንከባለል ቆይቶ ያልተፈፀመው ብዬ ስጠይቅ፣ አዎ እሱ ነው የሚል መልስ ተሰጠኝ፣ አንዳንዶቹ እንዳውም በዛ ጊዜ የነበሩ ሰዎች ናቸው አሉኝ፡፡ መጀመሪያ ላይ ተጠራጠርኩ፣ ጡረታ ላይ ነኝ ደግሞ አንድ የጀመርኩት መጽሃፍ ነበር እሱን አሁን አጠናቅቃለሁ ብዬ ነው የሄድኩት፣ ትልቁ ስራዬ እሱ ስለሆነ እሱ ላይ ለማተኮር ነው የማስበው አልኳቸው፣ ረጅም ነው ታሪኩ፣ ብቻ አብረን ቀጠልን መጨረሻ ላይ ስራውን ተቀበልኩ፡፡ አሁን እዛ ስራ ላይ ነው ያለነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዛ ሰዓት ባንክ ማቋቋም አይቻልም Great Recession የሚሉት ትልቅ Financial Crises ነበረ፣ ያኔ ፕሬዝዳንት ኦባማ ተመርጦ ቢሮ እንደገባ ትልቁ ስራው ሊፈርስ የነበረውን ያንን ኢኮኖሚ ማስተካከል ነበር፡፡ እ.ኤ.አ 1929 ፕሬዝዳንት ሩዝቬልት ሃገሩን በሚያስተዳድርበት ወቅት ትልቅ እንደዚህ ያለ Great Depression ተከስቶ ነበር፡፡ ብዙ ሰው ሥራ የፈታበት፣ ብዙ ሰው የተራበበት፣ ኢንዱስትሪዎች የቆሙበት፣ እርግጠኛ ነኝ በትምህርት ታውቁታላችሁ፣ እ.ኤ.አ ከ1929-1933 ለአራት ዓመታት የቆየ ሲሆን በስንት በስንተ ልፋት ትልልቅ ኢኮኖሚስቶች ተረባርበውበት መፍትሄ ያገኘ ነው፤ ኦባማም እንደምታውቁት ኢኮኖሚው መሻሻል ይችላል በሚል እምነት ብዙ ፕሮግራም ያወጣበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁንማ ባንክ ማቋቋም አይቻልም ተባብለን ቆይተን ባንኩን የምትመሰርት፣ አንድ ትንሽ ድርጅት አቋቋምን፣ እቺን ድርጅት ግን መመስረት እንችላለን ብለን 1 ሚሊየን ዶላር ካፒታል ያላት Ethiopian-American Investment Group የምትባል አቋቋምን፡፡ ከዛም ጥናት ስናካሂድ፣ ሌሎች ሥራዎችን ስንሠራ፣ ምን ስንል ቆየን፡፡ ከዛም እኛ ላሰብነው ዓይነት ባንክ እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል እንደሚያስፈልግ ተገነዘብን፡፡ አሁን ላይ ባንኮችን ለሚቆጣጠርና ፈቃድ ለሚሠጥ Federal Deposit Insurance Corporation የሚባል የአሜሪካን ፌዴራል መንግስት አካል ለሆነ ጥናቶችን አቅርበን፣ ጥናቶቹ ከሞላ ጎደል ታይተው፣ ትችትም ተደርጎባቸዋል፡፡ የእግዚሃር ፈቃዱ ከሆነ በዚህ ዓመት ውስጥ (Charter) ቻርተሩን እናገኝ ይሆናል፡፡ ባንኩንም በፈረንጆቹ በዚህ ዓመት መጨረሻ ወይም በሚቀጥለው ዓመት መጀመሪያ ላይ በአራት አምስት ወራት ውስጥ ማቋቋም እንደምንችል ነው የሚታየን፡ ፡ እንግዲህ አሁን አሜሪካን ሀገር በየከተማው እየሄድን ሼር ለመሸጥ ስድስት ሰባት ወር የሚሆን ጊዜ ነው የቀረን፡፡ አሁን ላይ Charter አላገኘንም፣ ካገኘን በኋላ ሼር እንሽጥ ብንል ግን በሀገራችን እንደሚባለው፣ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ነው፡፡ በችኮላ እንደሚሆን ነገር ማለት ነው፡፡ አሁኑኑ አስቦ መንቀሳቀሱ ይሻላል፡፡ ደግሞም ይህ የሚያሳስብ ነው፡፡ ባንክ ውስጥ ዛሬ ላይ Invest አድርጎ ነገውኑ ትርፍ አይገኝም፡፡ የረጅም ጊዜ የሙከራና የፈተና ጊዜ አለ፡፡ በማንኛውም ሀገር ባንክ ሲቋቋም ጥሩ ትርፍ ተገኝቶ ከመከፋፈሉ በፊት አራት አምስት ዓመትን ይፈልጋል፡፡ እና ይሄ አንዱ በቅድሚያ የሚታሰብበት ነው፡፡ እናም ምን አልኳቸው፣ የሸመገላችሁ ድንገት ላትደርሱበት ትችላላችሁ፣ ነገር ግን ለልጆቻችሁ ሊሆን ይችላል፡፡ ወጣቶች ደግሞ የምታዩት ነገር ነው፡፡ ግን አሁን አስቡ ሼር ስትገዙ ፣ ቡና ቤት ሄዶ ቡና እንደመግዛት አይደለም፡፡ አሁን ላይ ጠቀም ያለ ገንዘብ ነው የምታወጡት ቢያንስ ቢያንስ 10 ሺ ዶላር ነው የምንጠይቀው፡፡ ትልቁ (Maximum) ደግሞ 1 ሚሊን ዶላር ነው፡፡ ይህም ጥቂት ሰዎች ባንኩን Dominate አድርገው እኛን ሁሉ ሎሌ እንዳያደርጉን፣ በተቻለ መጠን Economic Democracy የሠፈነበት፣ Share Voting Power የተመጣጠነበት ባንክ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ በርግጥ Share Voting Power አንድ አይነት መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ፡ Maximum 1 ሚሊን ዶላር ነው ብያችኋለው፣ በ1 ሚሊዮን ዶላር ሼር የገዙ ሰዎች ከአስር፣ አስራ አንድ መብለጥ የለባቸውም ብለናል፡፡ ከዚያ የበለጡ እንደሆነ ደግሞ Majority ሆነው ያስቸግሩናል፡፡ ገዥዎቻችን ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ እሱንም አንፈልግም፡፡ እንደዚህ እየተጠነቀቅን፣ አንዳንድ ሰዎች ግን ከፍ ያለ ሼር እንዲገዙ እንፈልጋለን፡፡ የተቀረው ግን ከ 1ሚሊዮን ዶላር በታች 500 ሺ፣ 600 ሺ እያለ እየወረደ ሊገዛና በጣም ያልተራራቀ ድምጽ እንዲኖራቸው ነው፣ እነዛ ጥቂት ሰዎች Dominate የሚያደርጉ ከሆነ ፣ ያ ትንንሽ ድምጽ ያለው፣ ተልባ ቢንጫጫ በአንድ ሙቀጫ ነው፡፡ ይናገራል ነገር ግን የእነዛ የጥቂቶቹ ድምጽ ነው የሚጸናው፣ የሚተገበረው፡፡ አንድ ሰው በዕውነቱ የእኔ ባንክ ነው የሚለው ድምጹ ሲደመጥለትና ፣ ተናግሮ በተናገረው መሠረት አንድ ነገር ሲደረግለት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ እንግዲህ ህልም ነው፡፡ ህልማችን መቶ በመቶ ላይሳካ ይችላል፡፡ ህልም ማስቀመጥ ግን ያስፈልጋል፡፡ ፈረንጆቹ አንድ የሚሉት ነገር አላቸው፣ ፊልም ውስጥ በዘፈን መልክ ነው የወጣው፣ « ሕልም ያስፈልጋል፣ ሕልም ከሌለ እንዴት ወደ ተግባር ሊኬድ ይቻላል» የሚል ነው፡፡ ማንም ሰው ሕልም ያስፈልገዋል፣ እና ሕልማችን ይሄ ነው፣ ከሕልማችን ቀጥሎ ዓላማችን አለ፣ ዓላማችን ደግሞ ቅድም እንዳልኩት በተመጣጠነ ሁኔታ Economic Democracy የሠፈነበት ባንክ መፍጠር ነው፡፡ በዕውነት! ሁሉም ነገር በእግዚሃር እጅ ነው ያለው፡፡ እንደምታውቁት ሰው ደግሞ ሲያረጅ ወደ እግዚአብሔር እያዘነበለ ነው የሚሄደው፡፡ እኔ ደግሞ አሁን ወደ እግዚአብሔር እያዘነበልኩ ነው፡፡ በልጅነት ጊዜዬ እንኳን ከእግዚሃር ትንሽ እርቃለሁ፡፡ እና በአጠቃላይ ይህንን እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡ ወደ እዛ ስመለስ ያንን ሥራ እንቀጥላለን፡፡ እግዚሃር ካለ እንግዲህ ወደ ፊት የሥራውን ፍሬ የማይ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡ ይሄ አሁን አሜሪካን ሀገር እያቋቋሙት ያለው ባንክ ሼር ሽያጭ እዛ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ ነው ወይስ እዚህም ያሉ ሰዎች ሊሳተፉበት ይችላሉ?
መልስ፡ እንግዲህ በመሠረቱ እዛ ላሉ ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ በተለያየ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህንን ጥያቄ ጠይቀው ነበር፡፡ ማለትም ከአሜሪካን ውጪ በካናዳ፣ በእንግሊዝ ፣ እዚህም ያሉ ለምሳሌ እዚህ እና ውጪ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የሚሰሩ እንዲሁም አንዳንድ ባንኮች ጥያቄውን አንስተዋል፣ ውሳኔውን እኛ ማድረግ ስለማንችል ጥቄውን ለተቆጣጣሪው መሥሪያ ቤት አቅርበናል፣ ይቻላል ወይ አልናቸው አዎ በመሰረቱ የማይቻል ነገር የለም አሜሪካን ደግሞ ኢኮኖሚው ክፍት ነው ማንኛውንም ኢንቨስትመንት ይፈልጋል፣ ነገር ግን እያንዳንዱን ሼር የሚገዛውን ሰው ወይም ድርጅት በጣም በትኩረት ነው የምንመረምረው፣ በአሁኑ ጊዜ እንደምታውቁት Money Laundering የሚባል ነገር አለ፣ አክራሪ ሃይማኖት ተከታዮች፣ እንዲሁም አደንዛዥ ዕጽ የሚሸጡ ስላሉ ያ በዶላር የሚመጣው ገንዘብ የታጠበ ሳይሆን ንጹሕ ገንዘብ መሆን አለበት፣ በሳሙና ታጥቦ ከሌላ የመጣ ሳይሆን በትክክለኛው መንገድ የተገኘ መሆን አለበት አሉኝ። እኛ እስከ ምናውቀው ድረስ ይህንን ሼር እንግዛ የሚሉ ሰዎች ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፣ ደሞዛቸውን የሚከፍለው የተባበሩት መንግስታት ነው፣ የተባበሩት መንግስታት ደግሞ እኔ እስከ ማውቀው ድረስ እዚህ የምትሉት ዓይነት ንግድ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፣ ገንዘቡን የሚያገኘው መንግስታት ከሚሰጡት ነው፣ በዚያ ላይ የእነሱ ገንዘብ ደግሞ የሚቀመጠው በውጪ ሀገር ባለ ባንክ ነው፣ ስለዚህ በኔ አስተያየት እነዚህ ሰዎች ወይም ባንኮች ንግድ በመሆኑ ሊኖሩ ይችላሉ። አንተ ይህን እንደምትል ይገባናል፣ እኛም ደግሞ ከሞላ ጎደል እናዳምጥህ ይሆናል፣ ግን ጥያቄ ሲመጣ መመርመር አለብን ይሄ ገንዘብ ከየት መጣ፣ ምን ያህል ነው የሚለውን በሚገባ አስጠንቅቃቸው ብለውኛል ። ይሄንንም እያደረግኩ ነው ያለሁት እና አብዛኛው ገንዘብ የሚመጣው ከእዛ አካባቢ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ። እዛ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። የባንኩን መቋቋም በጣም የሚፈልጉ ደግሞ እነሱ ናቸው። የተወሰኑት ባንኩን የሚፈልጉት ደግሞ ለንግዳቸው ነው። ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን የተባበሩት መንግስታት ውስጥ የሚሰሩት እና እንዲህ ያሉት ባንኩን የሚፈልጉት ለገቢ ነው፣ ባሁኑ ጊዜ ገንዘብ ያላቸው ቢያስቀምጡ በወረደ ወለድ ነው፣ ወለድ ሰሞኑንም እየቀነሰ ይገኛል፣ ከቁጠባ ሂሳብ ምንም አያገኙም ማለት ይቻላል። አንዱ እንዳውም እንደዚህ ብሎኛል፣ አቶ ተካልኝ፣ እኔ 300 ሺህ ዶላር አለኝ ምን ላድርገው፣ ለሌላ ሰው እንደዚህ ብለህ አትናገር ምንም አያስፈልግም ግን የምትለው ይገባኛል። እኛም አሁን ድርጅታችን ውስጥ በትንሹ ካፒታል ማሰባሰብ ጀምረናል። እናም ያንን የምናስቀምጠው በ2% እንደዚህ ባለ ወለድ ነው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ትርፍ ለማግኘት ነው፣ በርግጥ ይሄ የተገባ ነው። ባንክ በመሠረቱ ትርፍ ማምጣት አለበት እና ቀደም ብለን የጀመርን ሰዎች አንድ ህልም አለን ያ ህልም እንደተጠበቀ ሆኖ ባንክ ባንክ ነው። ሼር የሚገዛ ሰው በ Dividend ይካሳል። እዛ ያሉ ሰዎች ግን የባንኩን ሼር የሚገዙት ትርፍ ለማግኘት ብቻ አይደለም ንግዳቸውን ሥራቸውን ለማስፋፋት ነው፣ የኢትዮጵያውያን ንግዶች እንዲስፋፋ። ለምሳሌ፡- አሜሪካ ላይ የኢትዮጵያ ምግብ እንደ ቻይና እና ሕንድ ምግብ ተወዳጅነት ያለው ነው፣ ነገር ግን የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንቶች ትንንሾች ናቸው፣ ተቆርቁዘው ነው የቀሩት፣ ምንድን ነው ይሄ የቻይና ሬስቶራንት የህንድ ሬስቶራንት ቆርቁዞ አይቀርም፣ ትንንሽ መካከለኛ እነዲሁም ትልልቆች አሉ የኢትዮጵያኖች ግን ትልልቆች የሚባሉት ደረጃ አልደረስንም እና አያድጉም ማለት ነው፣ ጥሩ ጥሩ ምግብ የሚያዘጋጁትን ግሮሰሪዎችም ሆኑ ሬስቶራንቶች ፈረንጆች ይወዷቸዋል፣ በተለይ ደግሞ የጾም ምግብ የሚሠሩትን፣ እንደምታውቁት ከ20-30 ዓመት የሠሩ ሬስቶራንቶች አሉ ግን ዕድገት አያሳዩም ። አንድ ነገር ቢጐድል ነው፣ ድንገት ከጐደለው መሐል ደግሞ ይሄ ባንኩ ነው ብለን ገምተናል። ጥያቄ፡ አሁን ከሚናገሩት እንደምንረዳው ይሄ አሁን የሚያቋቁሙት ባንክ ከባንካችን አቢሲንያ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ነው መቼም? መልስ፡ አዎ እንዳዉም Correspondent ባንክ እንዲሆን ከሌሎች ጋር አወዳድረን አቢሲንያ ባንክን መርጠናል ይሄ አንዱ ነው ወደ ፊት ደግሞ ሥራችን እየሰፋ ሲሄድ ሌሎቹም ባንኮች ዕድል ያገኛሉ፣ ለጊዜው ግን የመረጥነው አቢሲንያ ባንክን ነው፣ ትንሽም MoU ነገር ተፈራርመናል፡፡ ይህ ግልፅ የሆነ ነገር ነው። በግልፅ አወዳድረን ነው አቢሲንያ ባንክን የመረጥነው። ከሌሎች ባንኮችም ጋር ወደ ፊት አብረን እንሠራለን። እግዚአብሔር ካለ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች አፍሪካ ሀገሮችም እንሄዳለን። ድንገት ያሰብነውን ያህል ካፒታል ባናሰባስብ ጐረቤት ሀገር ያሉ ሰዎች አሜሪካን ሀገር ያሉ Diaspora የኬንያ ሰዎች ኤርትራዊያኖች ሱዳኖች፣ ልዩ ሀገር ናቸው ነገር ግን እኛ በእዛ ዓይነት መንፈስ አንመለከታቸውም። አክሲዮን እንዲገዙና ይህ ኢትዮጵያኖች የሚያቋቁሙት ባንክ የእኛም ባንክ ነው ብለው እንዲያስቡ ነው የምንፈልገው፣ እንግዲህ ወደ ፊትም ወደ ሀገራቸው ሊገቡ ይችሉ ይሆናል፣ ይህ እንግዲህ ከእኔ በኃላ የሚመጣ ነገር ነው። ይሄ የጀመርነው ባንክ ቢቋቋም ታሪካዊ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም እስካሁን ድረስ ማንኛውም የአፍሪካ ሀገር የግብፅ የደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የናይጄሪያ Immigrants/Diaspora ነው የሚባለው፣ ማንም ባንክ አላቋቋመም፣ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ይሄንን ሲያቋቁም በአሜሪካን ሀገር ውስጥ የመጀመሪያው ነው። ይሄ ደግሞ የተገባ ነው ከኢትዮጵያ ታሪክ ባህል ጋር የሚሄድ ነው። የኢትዮጵያ ስም ጥሩ ስም ነው፣ ኢትዮጵያ ያለምክንያት አይደለም ይሄን ያክል ዘመን ነፃ ሆና ትልቅ ሀገር ነኝ የምትለው የምትኩራራው፣ እንዲህ ያለ ሥራ መሥራትም ትችላለች ማለት ነው፣ ስለዚህ ይህን ብንሠራ ታሪካዊ ባንክ ብናቋቁም ለታሪካችን የተገባና የሚጠበቅ ነው። ከታሪካችን ከባህላችን ከማንነታችን ጋር አብሮ የሚሄድና የሚመጣጠን ተግባር ነው የሚሆነው፡፡
Leave a Reply