ገንዘብ ምንድን ነው?
ቀደም ባሉት ጊዜያት እንደሚታወቀው ሰዎች ግብይታቸው ቁስን በመለዋወጥ ወይም ዕቃን በዕቃ በቀጥታ መለዋወጥን መሰረት ያደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ነበረ፡፡ ይህ ማለት አንድ ሠው ዕቃ ለመሸመት ከፈለገ፤ ያን የፈለገውን ዕቃ የሚያቀርብለትን አካል ወይም ግለሰብ ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል ተለዋጭ ዕቃ ይዞ መገኘት እና መቅረብ የግድ ይለው ነበር፡፡ ይህ በምጣኔ ኃብት አነጋገር – የጥምር ፍላጎት ግጥምጥሞሽ ወይም ክስተት (Double Coincidence of Wants) ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ ግብይት እጅግ ከባድ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ በመሆኑም ቀስ በቀስ ሌላ የግብይት ስርዓቱ አቀላጣፊ በማስፈለጉ ምክንያት በራሳቸው ዋጋ ያላቸው ቁሶች ጉልህ ሚናቸውን መጫወት ጀመሩ እንደምሳሌ ያህል፤ ወርቅ፣ ብር እና የመሳሰሉትን ሲሆኑ እነዚህም ቁሶቹ ከገንዘብነት ባለፈ ለሌላ ጉዳይ እንዳስፈላጊነታቸው በተፈጥሯቸው የተነሳ አገልግሎት ላይ መዋል ይችሉ ነበር ወይም ይችላሉ፡፡ በሂደት ግን ይህም አሰራር ተቀይሮ ለብቻው በራሱ – ገንዘብ – ሆኖ ከማገልገል ውጭ ዋጋው ኢምንት የሆነ፤ መንግስታት አትመው ወይም አሳተመው ስርጭቱን እንዲሁም ተመኑን የሚያስቀምጡለት ሰርዓት ተፈጠረ እሱም አሁን የምንገለገልበት – የወረቀት ገንዘብ፣ ሳንቲም እና ወዘተ ናቸው፡፡ ይሀም Fiat Money የሚባለው እሱም በመንግስት ዕውቅና እንዲሁም ድንጋጌ ስር ያለ ገንዘብ እንደማለት ይሆናል፡፡
ገንዘብን ለምን እንጠቀምበታለን?
በመሰረቱ ከላይ የገንዘብን ጠቀሜታ ስንመለከት የዘረዘርናቸውን ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሦስት ያሉትን የሟላ ማንኛውንም ነገር እንደገንዘብ ልንወስደው የማንችልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም፡፡ ይሀን የምልበት ምክንያትም ታሪክን ስንመለት የምንረዳው በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ልዩ ልዩ ይዘቶች ወይም ደግሞ ቅርፆችን ሊይዝ የሚችል ሲሆን፤ በዋናነት ግን እንደሚከተለው ሊገለፁ ይችላሉ፤ እነሱም – ከላይ ለመዳሰስ እነደሞከርኩት አንደኛው – ዕቃው/ቁሱ በራሱ ዋጋ ያለው (Commodity Money), ሁለተኛው ደግሞ በራሱ ነጥሎ እሴቱ (Unique Value) ይሄ ነው ለማለት ከሚያስደፈር ደረጃ ጋር ሲነፃፀር ምንም የሆነ ወይም ኢምንት የሆነ መንግስታት ዋጋ የሚያወጡለት (Fiat Money) ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ አሁን አሁን የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ በፈጠረው መልካም የገበያ ትስስር የዘመናችን አዲስ አይነት ገንዘብ እየተዋወቅን እንገኛለን እርሱም ከሪፕቶከረንሲ ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡
በነገራችን ላይ ገንዘብ ብለን የምንረዳቸውን መጠሪያዎች (Currency and Money) ለያይተን መመልከት የሚያስፈልገን እዚህ ላይ ነው፤ አንደኛው (Money) የማይዳሰሰ በቁጥር ብቻ የምንገልፀው ሲሆን፤ ሌላኛው(Currency) ግን የሚጨበጥ በኪሳችን የሚገኘው ሳንቲምና ላመንጪው እንዲከፈል የሚያስገድደው የባንክ ወረቀት/ቅጠል ነው ለምሳሌ የሀገራችን ብር፣ የአሜሪካ ዶላር፣ የሩሲያ ሩብል እና ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በመሰረቱ ብዙውን ጊዜ ሁለቱን እያቀያየርን ነው የምንጠቀማቸው፡፡ በጥቅሉ ወደ ዋና ጉዳዬ ስመለስ፤ ገንዘብ ተብሎ የምንሰይመው ነገር እንደየዘመኑ የተለያየ ይዘት ወይም ቅርፅ በአንድ ሀገር ውስጥ ሲውል ከታሪክ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ግለሰቦች አልያም የንግድ ተቋማት ደግሞ ድንበር ዘለለ ግብይት ለመፈፀም ሲሉ የገንዘብ ልውውጥ ያስፈልጋቸውል፡፡ እናም የአንድ ሀገር ገንዘብ ወደ ሌላ ሀገር ገንዘብ መለወጥ የገንዘብ ምንዛሬ እንለዋለን፡፡
የሀገራት ገንዘብ የራሳቸው የሆነ የውስጥ ንግድ አስናባሪ ወይም ድልድይ በመሆን ያገለግላል፡፡ ልክ በእኛ ሀገር ብርን ቁጥጥር የሚያደርግበት የኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ እንደሆነው፤ በሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ ማዕከላዊ ባንኮች ተመሳሳይ ተግባርና ኃላፊነት ተሰቷቸዋል፡፡ እንደሚታወቀው ሀገራት የተለያየ የኢኮኖሚ መሰረት፣ የሠው ኃብት፣ የተፈጥሮ ኃብት፣ መልካአምድራዊ አቀማመጥ፣ የባህል ስብጥር እና ወዘተ የገንዘብ ምንዛሬአቸው ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ ያሳድሩባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በሳዕዲ አረቢያ የነዳጅ ምርት፣ በህንድ ደግሞ የጨርቃጨር ወይም የሩዝ ምርት ዋጋዎች በሚጫወቱት ሚና እነዚህ ሀገራት የየራሳቸው ገንዘብ ኑሯቸው እንዲገኙ ብሎም ተመንም እንዲቆርጡለት ሲደረግ ይታያል፡፡
እዚህ ላይ አስገራሚ ምሳሌ ለማንሳት ያህል የአውሮፓ ህብረትን እንመልከት፡፡ የህብረቱ አባል ሀገራት አብዛኞቹ በንፅፅር ሲታዩ አነስተኛ የቆዳ ስፋት እንዲሁም ተቀራራቢ የባህል መሰረት ብሎም ዲሞግራፊ ይስተዋልባቸዋል፡፡ በዚህና ምናልባትም በሌሎችም ምንክንያቶች ከላይ እንደምሳሌ የተነሱትን ሀራት በመሰለ አኳኋን የየራሳቸወን ገንዘብ በነጠላ ከመጠቀም እና ከመመንዘር አንድ አይነት ገንዘብን ቢጠቀሙ የሚቀላቸው ሆኖ በማግኘታቸው ይህንን መጠቀም ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ የህብረቱ ሀረገራት በዋናነት አንድ ዓይነት ገንዘብ መጠቀማቸው ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንዲሁም በቀጥታ የዕርስ በዕርስ የንግድ ልውውጥን ስያጎለብተው ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ የራሱ የሆነ ክፍተትን እንዳለው በቅርብ ጊዜ ለማስተዋል ተችሏል፡፡ ይህም የግሪክን የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ የተጋረጠባቸው ፈተና ነው፡፡ አንዱ ደካማ በሌላኛው ብርቱ ጫንቃ ተወዝፎ መጓዝ መንገዱን አድካሚ ብቻም ሳይሆን ተስፋ በማስቆረጥ የግልን ምርጫ እስከ መከለስ ሊያደርስም ይችላል፤ ይህ ነው በአውሮፓም የታዘብነው፡፡
የገንዘብ ምንዛሬ ተመን
የገንዘብ ተመንን ስንመለከት በዋናነት ሁለት መንገዶችን እናገኛለን፡፡ አንደኛው ተዘዋዋሪ/ተንሰፋፊ የገንዘብ ምንዛሬ ተመን /floating exchange rate/ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ቋሚ የምንዛሬ ተመን /Fixed Exchange rate/ የሚባሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ዓይነት አተማመን ገበያውን ተከትሎ ከፍና ዝቅ በማለት የሚዋዥቅ ሲሆን፤ ሁለተኛወ ዓይነት ደግሞ በተቃራኒው ከሌላ ሀገር ገንዘብ አንፃር ምንዛሬው ተተምኖ በቋሚነት የሚቀመጥ ይሆናል፡፡ሁለቱም አተማመኖች የየራሳቸው በጎም መጥፎም ጎን አላቸው፡፡ የተንሳፋፊን የምንዛሬ ተመንን ያየን እንደሆነ፤ አንድ ገንዘብ እጣፈንታው የሚወሰነው ዓለም አቀፋዊ በሆነ የገበያ ጠባይ ሲሆን፤ ማለትም የገንዘቡ መዳከምም ይሁን መጠንከር ማዘዝ ከሚቻልበት ድንበር የሚሰፋና የገዘፈ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በአሜሪካ፣ በህንድ እንዲሁም የይሮ ቀጠና ማንሳት ይቻላል፡፡ቋሚ የምንዛሬ ተመንን ስንመለከት፤ የዚህ አካሄድ መገለጫ ሀገራት የዕለቱን የምንዘሬ ተመን ገበያውን ተመርኩዘው ቁርጥ ተመን በማስቀመጥ ይሆናል፡፡ ቻይና በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ሀገር ናት፡፡ ከአኽጉራችን አፈሪካ ደግሞ አንዳንድ ሀገራት ይህንን ሲከተሉ፤ ሀገራችን ኢትዮጲያ ይህንን ስትከተል የነበረቸው በቀድሞ የመንግስት ስርዓት ነበር፡፡የገንዘብ ምንዛሬ ተመን አንዱና ዋንኛው የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ጤንነት ማሳያ ወይም መለኪያ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ምንም እንኳ በጥንቃቄ መተንተን በያስፈልገውም፡፡ የምንዛሬ ተመን በጥቅሉ የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ዑደትን እና እንቅስቃስን ለመመለክት የሚያግዝ ሁነኛ መሳሪያ ነው ይባልለታል፤ ለዚህም ሲባለ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህንን ቁልፍ ነገር ይተንትናሉ፣ ይገመግማሉ እንዲሁም ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ አንድ ሰው የውጭ ምንዛሬን ያሰበ እንደሆነ መቼም ተመኑን ልብ ማለቱ የግድ ነው፡፡ቀደም ብለን እንዳየነው የምንዘሬ ተመን ማለት ሀገራት መሃል በሚደረግ ግብይት ወይም የገንዘብ ልውውጥ ጠቋሚ አልያም መለኪያ መሳሪያ ነው፡፡ ይህም እንደምሳሌ የኢትዮጵያ ብር በንፅፅር ከሌሎች ሀገራት ገንዘብ ሲቀመጥ የሚገኘው ምጣኔ ማለት ነው፡፡ በመሰረቱ ይህ ተመን በየዕለቱ ሊለዋጥ ይችላል ማለትም የሌላ ሀገር ገንዘብ ፍላጎትና አቅርቦቱ በአንደ ሀገር የገንዘብ ትመና ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ስላለው፡፡ ስለሆነም የምነዛሬ ተመንን መረዳት ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴን ለሚያደርጉ ሆነ ለሀገር ውስጥ የንግዱ ተዋንያን ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡ የምንዛሬ ትመናን ወሳኝ ከሆኑት ቁልፍ ነገሮች ውስጥ የተወሰኑትን ለማንሳት ያህል፤
- የዋጋ ግሽበት (Inflation factor) ፡ የዋጋ ግሽበት መጠን ለውጥ የምንዛሬ ተመን ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ በንፅፅር ዝቅተኛ የዋጋ ግሽበት መጠን ያለው ሀገር የሚጠቀምበት ገንዘብ አቅሙ እየጠነከረ ዋጋውም እየጎለበት ይታያል፡፡ በእነዚህ ሀገራት የአገልግሎትም ሆነ የዕቃ ዋጋ ዝቅተኛ በሆነ ሂደት ብቻ ጭማሪን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት መጠን የሚታይበት ሀገር የገንዘቡ ዋጋም እየተዳከም እንዲሁም የወለድ መጠን መጨመርን ያስከትላል፡፡ በመሆኑም ዋጋ እየናረ ያለበት ሀገር የገንዘብ የመግዛት አቅሙ ይቀንሳል በተመሳሳይ ደግሞ በሀገር ውስጥ ገንዘብ መዳከም የውጭ ሀገር ገንዘብን ደግሞ አቅም ጠንክሮ ይታያል፡፡
- የክፍያ ሚዛን (Balance of Payments)፤ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የንግድ ጉድለት አላቸው ማለት ከሚያስገቡት ወይም ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ የሚከፍሉት አሊያም የሚያወጡት የውጭ ምንዛሬ ከፍ ያለ ነው ማለት ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት የምንዛሬ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣነ በመኖሩ የምንዛሬ ተመንን ያሳድገዋል በዚያው ልክ ደግሞ የገንዘብን አቅም ያዳክማል፤
- የወለድ ተመን፡ በግልፅ እንደሚስተዋለው የወለድ ተመን ለውጥ ወይም ማሻሻያ ከሀገርን የገንዘብ ምንዛሬ ተመን ጋ ቀጥተኛ ቁርኝትን ያሳያል፡፡ የወለድ መጠን የሚያመለክተው የብድር ትርፍና ወጪውን ነው፡፡ ትንሽ ሃሳቡን ለማፍታት ያህል፤ የሀገር ውስጥ የወለድ ተመንን ከውጭ ካለው አንፃር ማሳደግ የሀገር ውስጥ ገንዘብን ፍላጎት ያሳድገዋል፡፡ በሌላ አባባል የወለድ ተመንን ከፍ ማድረግ የአንድን ሀገር ገንዘብ አቅም ያጎለብታል ምክንያቱም ከፍተኛ የወለደ ተመን ኖረ ማለት አበዳሪዎች ፍላጎት ኖራቸው ማለት ነው ይህ ደግሞ የውጭ ካፒታል ፍሰትን ይጨምረዋል የዚህ ውጤት ደግሞ የምንዛሬ ተመንን ማሳደግ ይሆናል፡፡
- የመንግስት የብድር/ዕዳ መጠን፡ ይህ ማለት የህዝብ ዕዳ አልያም ብድር ማለት ሲሆን የሚመለከተውም ማዕከላዊ ባንክን ይሆናል፡፡ ባለሀብቶች ከፍተኛ የዕዳ መጠን የሚያይበት ሀገር አይመርጡም፡፡ ሌላው ቀርቶ ዕዳ ሊጨምር ይችላል እንኳን ተብሎ ከተተነበየ የያዙትን ሽጠው መገላገልን ይመርጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ የምንዛሬን አቅም ወይም መጠን በእጅጉ ያወርደዋል፡፡
- የፖለቲካ መረጋጋት ወይም ሁኔታ፡ አንዱ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ቁም ነገሮች ውስጥ የሀገር ፖለቲካዊ መረጋጋት በጎ ጎን ወይም አበረታች ተፅዕኖን መፍጠሩ ነው፡፡ የተረጋጋች ሀገር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ትማርካለች፡፡ ይህ ማለት የውጭ ካፒታል ፍሰቱ ይጨምርና የሀገሪቱ ገንዘብ አቅም ይጎልብታል ማለት ነው፡፡ ፖለቲካው ሲረጋጋ ግልፅ እንዲሁም አስተማማኝ የፋይናንስ እንዲሁም የንግድ ስርዓት ይሰፍናል፡፡
- የመንግስት ገብያ ላይ ያለው ጣልቃ ገብነት፤ ዓለም አቀፋዊ ግብይት ላይ አንደ ሀገር የሚዋዥቅ የምንዛሬ ተመን ከታየባት፤ አንድም መዘዙን በመፍራት አሊያም መንግስታት ያስቀመጡትን ፖሊሲ ዕውን ለማድረግ በማሰብ የተመን ማስተካከያ ሊያደርጉም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በከፍተኛ ደረጃ የምንዛሬ ግዢና ሽያጭ ላይ በቀጥታ ይሳተፋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዘሬ አቅርቦትና ፍላጎ መለወጡ የምንዛሬ ተመኑ ላይም ለወጥ ያሳያል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ሃሳብ ላካት እሱም የግዥ ኃይል መመጣጠንን (Purchasing Power Parity /PPT/) ነው፡፡ ይህ ሃሳብ የሚያመላክተው የሁለት ሀገራትን የገንዘብ ተዛምዶ ከሚለዋወጧቸው ቁሶች ጋር መመልከት ነው፡፡ መመጣጠን ስንል እንድን ምርት በዓለም ዓቀፋ ንግድ መድረክ ላይ ተመሳሳይ ገንዘብን ተመርኩዘን ስንለካው ተመሳሳይ የዋጋ ልኬት ሊኖረው ይገባል ማለት ነው የሚል ሃሳብ ነው፡፡
ስለዚህ በጥቅሉ ከላይ ያሉት እንዳሉ ሆነው፤ የምንዛሬ ተምን ከሌላ ገንዘብ አንፃር ወሳኝ የሚሆነው በሚስተዋለው የፍላጎትና አቅርቦት መጠን ላይ ተመርኩዞ ይሆናል፡፡ ማለትም መጀመሪያ የገንዘብ ፍላጎት የሚመነጨው ሠዎች የአንድን የውጭ ሀገር ዕቃ/አገልግሎት ለመግዛት ሲሹ ነው፡፡ እንደ ሀገር ደግሞ የምንዛሬ ተመንም ወደ ውጭ ከሚላኩና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡት ላይ የተመሰረት ይሆናል፡፡ የወጪ ንግዱ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚያስገባው የበለጠ የሆነለት ሀገር፤ የገንዘብም ተፈላጊነት መጠን የሚያድግ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የወጪ ንግዳቸው ሚዛን የሚያነሳላቸው ሀገራት፤ በሀገር ውስጥ ገንዘባቸው ለሽያጫቸው ክፍያን ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ ሌላኛው የገንዘብ ፍላጎት ደግሞ፤ ከወለድ ምጣኔ ና ከፋይናስ ገበያው የሚመነጭ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ሆን ተብሎ የሚዳከምበት አካሄድ አለ፡፡ ለዚህም እንደምክንያት የሚነሳው ወደ ሀገር የሚገቡትን ዕቃ/አገልግሎት አስወድዶ ወጪ ንግድን በዝቅተኛ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ብርቱ ተፎካካሪ እንዲሆን ማስቻለ ነው፡፡ እርግጥ እነዚህ ነጥቦች ሁሉንም ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ባያካትቱም ነገር ግን በግንባር ቀደምትነት ተደጋግመው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የገንዘብ ነገር
እንበልና አንድ የአሜሪካን ዶላር በሁለት የኢትዮጵያ ብር ቢመነዝር ዛሬ ላይ ሁነን ምን ማለት ይሆን? ይህ እንግዲህ በሀገራችን በ 80ዎቹ ላይ የተመነዘረበትን ዛሬ ላይ ብናመጣው እንደማለት ነው፡፡ እናም ይህ ማለት በቀላል ቋንቋ የሀገሪቱን እዳ በአንድ ጀንበር ገንዘብ በማተም እዳዋን ለመክፈል እንደማሰብ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ የአንድ ሀገር ገንዘብ ምንዘሬ ተመን የግድ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ጥንካሬ ሊያሳይ አይችልም፤ ለዚሀም ነው ቀደም ብዬ የምንዛሬ ተምንን ስንተነትን በጥንቃቃ ቢሆን ያልኩት፡፡ እንደውም አንዳዶች የገንዘብ ምንዛሬ ተመን ከሀገር የኢኮኖሚ ጥንካሬ ጋር የረባ ትስስር አይታይበትም በማለት ይልቅ የውጭ ምንዛሬ ተመን ተፅዕኖ የሚያድርበት በንግድ የአፈፃፀም አቅም፣ በካፒታል ፍሰት ወይም እንዲሁ በተዛማጅ ጉዳዮች ሊቀምጥ መቻሉን በማንሳት ኃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡
እናም የሀገራችን ገንዘብ 1፡2 የአሜሪካን ዶላር/ብር ሬሾ ቢተመን፤ እንደምሳሌ – የቅንጦት ዕቃዎች በርካሽ መገብየት ሲቻል፣ ነዳጅን ጨምሮ ሌሎች ከውጭ የሚገቡ ምርትና አገልግሎቶችም በርካሽ ለሀገር ውስጥ ተጠቃሚ መቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በጎ በጎውን ስናወሳ ነው፡፡ ነገር ግን ሀቁ ወይም እውነታው የሚሆነው የተለየ ነው፡፡ ወጪ ንግድ በዚህ የተመን ልኬት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ውድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጲያን ምርቶች ዋጋቸው ተወዳዳሪ ወይም ሳቢ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ሌላው የውጭ ሀገር ኢንቨስትመን ይዳከማል፡፡ ስለሆነም ለእንደኛ አይነት ሀገር እንዲህ ያለ እርምጃ መዘዙ በዙ ይሆናል፡፡
ምን አልባት ከዚህ አይነት ተፅዕኖ ለመውጣት ሀገሪቱ እራሷን በራሷ ሙሉ ለሙሉ ፍላጎቷን ለማሟለት በትሞክርስ ያልን እንደሆነ፡፡ መሰረታዊ የግብይት ፅንሰ ሀሳብ ስተናል ማለት ነው፡፡
የገንዘብ አቅም መዳከም
ሀገራት ለምን የገንዘባቸውን አቅም ያዳክማሉ?
- ወጪ ንግድን ለማበረታታት፤ እንደሚታወቀው ዓለም አቀፍ ንግድ በውድርድር ነው፡፡ በዝቅተኛ ዋጋ ገበያውን መወዳደር ደግሞ አንዱ የንግድ ስልት ወይም መንገድ ነው፡፡ ገንዘቡን ያዳከመ ሀገር ላኪዎችን በዓለም አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ ሲያደር ገቢ ንግድን ግን ይቀንሳል ወይም አያበረታታም ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ተደጋግሞ እንደሚታየው ይህ ዘዴ ወጪ ንግድ በሂደት ለዓለም አቀፍ ገበያ ያቀረበው ምርት ወይም አገልግሎት ፍላጎት በመጨመሩ የተነሳ ቀስበቀስ በተዘዋዋሪ ዋጋውም እየተሻሻለ ይመጣል፤ በሚል እሳቤ የሚወሰድ እርምጃ ነው፡፡ በመሰረቱ ይህ እርምጃ የንግድ ጦርነት እንዳይቀሰቅስ ውሳኔ ወይም አካሄዱ ብልሃትን ያሻዋል፡፡ ሆን ተብሎ የሚደረግ ከሆነ ማለት ነው፡፡
- የንግድ ጉድለትን ለማሻሻል ፡ ማለትም ወጪ ንግድ ሲጎለብት በተቃራኒው ወደ ሀገር የሚገቡት ዕቃዎች/አገልግሎቶች ውድ እንዲሆኑ በመደረጉ፤ እያደር ሚዛኑ መልካም ደረጃ ይደርሳል፡፡ ይህ ግን አሉታዊ ጎንም አለው፡፡ ማለትም ልክ እንደ እኛ ያለ ድሀ ሀገር በውጭ ሀገራት ገንዘብ የሚቀመጥ ብድርን ወይም ዕዳን ከሀገር ውስጥ ገንዘብ ተምን አንፃር ሲሰላ እጅግ ያልቀዋል ወይም ዕዳው ያብጣል፡፡
ብዙ ጊዜ የወጪ ንግድን የሚያበረታታ ፖሊሲን የያዘች ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገቷም ላይ አውንታዊ ተፅዕኖ ማምጣት ይቻላታል፡፡ በዋናነትም በወጪ ንግድ ላይ የተቃኘ ኢንዱስትሪ ከፍ ያለ የአምራች ኃይል አቅምን ያሳያል ይህ ደግሞ የተሻለ ደመወዝ ለሠራተኛው ክፍያን መፍጠር ይችላል ማለት ነው፡፡
በጥቅሉ አንድ እንዲታይ የምሻው ጉዳይ፥ የገንዘብ አቅም መዳከም ከወጪ ንግድ ጋር ያለውን ዝምድና በተመለከተ የተለያዩ ኃሳቦች በዘርፉ ሙሑራን እንደሚስተዋል ነው፡፡ አንዳንዱ የሚዋዥቅ የገንዘብ ትመና የሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገትም ሆነ ኢነቨስትመንትን ይጎዳል ይህም ሲባል ወጪ ንግድንም ጨምሮ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የለም ተፅዕኖ ሌላም መልክ ይኖረዋል የሚሉ ይገኛሉ ፡፡
ተጠባባቂ የውጭ ምንዛሬ (መጠባበቂያ)
ቀደም ብለን የውጭ ምንዛሬ ተመንን እንዲሁም ጠቅላላ አመጣጡን በአጭሩ ተመልክተናል፡፡ ይህንን ነጥብ አብረን የማንዘነጋው ጉዳይ ጋር ያደርሰናል፤ እሱም የውጭ ምንዛሬ መጠባበቅያ፡፡
የውጭ ምንዛሬ መጠባበቅያ የምንለው በመሰረቱ በመንግስት የሚያዝ የውጭ ምንዛሬን ለማመላከት ነው፡፡ የምንዛሬንም የመረጋጋት መጠንን የሚያመላክት ሆኖ ይወሰዳል፡፡ ማለትም የዋጋ ንረትንም ሆነ የገንዘብ ቀውስን ሊከላከል የሚችል መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ እርግጥ የዚህ ፁሑፍ ቁልፉ ጉዳይ በአጭሩ መሠረታዊ ነጥቦችን መዳሰስ በመሆኑ ጠለቅ ብለን ኃሳቡን ለማየት ምንአልባት በሌላ ፁሑፍ የምንገናኝ ይሆናል፡፡
ከላይ እንደተመለከትነው በቋሚ የምንዛሬ አተማመን ዘዴ የገንዘብ የድጋሚ ስሌትን እና ዋጋ መቀነስን እንደ ይፋዊ የአንድ ሀገር የገንዘብ በንፅፅር መገለጫ አልያም መተመኛ አድርገን የምንመለከትበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተንሳፋፊ ያልነውን ዘዴ የሚጠቀሙ ገበያው በሚፈጥረው ኃይል አማካኝነት የገንዘብን አቅም ያዳክማል ወይም ደግሞ ያጠነክራል፡፡
የመጠባበቂያ ገንዘብ በማዕከላዊ ባንኮች ወይም የሚመለከተው የገንዘብ ነክ/ጉዳይ ባለስልጣን እንዲያዝ ሲደረግ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የውጭ ምንዛሬ ሊቀመጥ ይችላል፤ ምንም እንኳን በአብዛኛው የሚያዘው በአሜሪካን ዶላር ቢሆንም፡፡ በመሆኑም በመሰረታዊነት የውጭ ምንዛሬ መጠባበቅያ ስንል የሚያመለክተው በውጭ ሀገራት ገንዘብ፣ ከሀገር ውጭ ባሉ ባንኮች የሚገኝ ተቀማጭ ገንዘብ፣ የውጭ የግምጃ ቤት ሠነድ እና መሠሎቹን ነው፡፡ ነገር ግን ቃሉን በይበልጥ የሚስተዋለው የወርቅ ተቀማጭን እንዲሁም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የመጠባበቅያ ልኬትን አካቶ ሲነገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው ከብሪቶነ ዎድስ ይዘት ወይም አሰራር ወዲህ በርካታ ሀገራት ተለዋዋጭ የምንዛሬ አተማመንን ተቀብለዋል፡፡ ይህ ማለት የውጭን ምንዛሬ ጉዳይን በመጠባበቅያ ቀደም ብሎ እንደሚያዘው ሊሆን አይገባውም ነበር፤ ምንም እንኳን እውነታው ይህ ባይሆንም፡፡
ሌላው ልናነሳው የምንችለው ነጥብ የ ጄ እጥፋት ክስተት ነው፡፡ ይህ ክስተት የምንዛሬ ተመን በረዥምና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ለመመልከት ነው፡፡ ለዚህ እንደ ማብራሪያ የሚነሳው ጉዳይ የምንዛሬ ተመን የሚያሳየው የለውጥ እንቅስቃሴ በሀገር ከሚከወነው የንግድ መጠነ (በቁጥር ማለት ነው) ጋር ሲነፃፀር ተመኑ ላይ ዝግ ያለ ጭማሪ አልያም ለወጥ የሚስተዋል በመሆኑ ነው፡፡ ከላይ በተወሰነ ደረጃ እንደዳሰሰኩት የገቢና ወጪ ንግድ ጉዳይ የምንዛሬ ተመን ቀጥታ የሆነ ተፅዕኖም አስተዋፆም ይኖረዋል፡፡
መደምደሚያ
የትኛውንም ትመናን ወይም ዋጋን ለመወሰን በቀዳሚነት የምንገነዘበው ጉዳይ በልዋጩ ምንን አገኛለሁ የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ወይም ይህንን ለማግኘት ምንን መተው ይኖርብኛል የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ የገንዘብም ትመናም እንዲሁ ነው፡፡ ማለትም ገንዘብ እንደማንኛውም ቁስ መለዋወጫ ተደርጎ ቢወሰድ ማለት ነው፡፡
መሠረታዊው ነገር የውጭ ምንዛሬን ጉዳይም ሆነ የገንዘብን ጉዳይ በበርካታ መልኩ ልንዳስሰው፣ ልንተነትነው እንዲሁም ልንፈትሽ እንችላለን፡፡ በጥቅሉ ግን የገንዘብ ቁም ነገር ከሀገር ውስጥ ጉዳይ መሻገሩ ላይ ነው፡፡ ማለትም ድንበር ዘለል ንግድ እና የውጭ ምንዛሬ በሊሂቅ ምጣኔ ኃብት ዘርፍ የሚዳሰስ ነገር ሆኖ፤ የሀገርን የንግድ ሚዛንን እንዲሁም የክፍያ ፍሰት ሚዛን አትኩሮት የሚሰጣቸው ነገሮች በአንድ ማዕቀፍ ብቻ ሊቀመጡ ስለማይችሉ ነው፡፡
የገንዘብ ምንዛሬ ቁልፉን ሚና የሚጫወቱት ወይም ትልቁ ሃሳብ የገቢና ወጪ ንግድ የሚያሳዩት ልዩነት ወይም መበላለጥ ነው፡፡ ሌላኛው የሚሠመርበት ጉዳይ ደግሞ የገንዘብ ፍላጎት እና አቅርቦት ያላቸውን ሚና ነው፡፡ ለምሳሌ የሀገራችን ፍላጎት ከሚገኘው የአሜሪካን ዶላር ጋር ያለውን ቁርኝት ወይም ዝምድናን ስንፈትሽ የምናገኘው ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ታዲያ የሀገራትን የገንዘብ አቅም ወይ መዳከመ አልያም ጥንካሬን የሚያሳይ ልኬትን የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ለማጠቃለያ ያክልም አሁን በሚታወቀው ደረጃ አራቱ የምንዘሬ ተመን ተፅዕኖ ፈጣሪ የምንላቸው፤ ፍላጎትና ምርጫ፣ ገቢ፣ የዋጋ መጠን እንዲሁም የወለድ መጠን ናቸው፡፡ በብዙ ረገድ ብናየው ቀደም ብየ እንደገለፅኩት በተለያዩ ሁኔታዎች የገንዘብ አቅም መዳከም ወይም መጠንከር በራሱ መጥፎም ጥሩም ሊሆን አይችሉም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ ጉዳይ ሊይዘን ብሎም ሊያሳስብን አይገባም በማለት አልያም ይህን እንደ አንድ ተግዳሮት በመታየቱ ወጥ የመገበያያ ገንዘብ ጥቅም ላይ ማዋልን የሚያበረታቱ አሉ፤ እንደ ኤሮ ገንዘብ ማለት ነው፡፡ ምስራቅ አፍሪካም ብሎም መላው አሁጉሩችንም ወጥ ገንዘብ ለመጠቀም የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ከተጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ የገንዘብ ጉዳይም አሁን ከምንመለከተው ወይም ከተለማመድነው ባህሪ ውጭ ያለውን የማየት ዕድላችን ሠፊ ነው፡፡
ርስቱ ፍቃዱ ተ.
Leave a Reply