አቢሲንያ ባንክ የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱን በሚሰጥበት አቢሲንያ አሚን በኩል አዘጋጅቶት የነበረው ሁለተኛው ዙር አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር በርካታ ተወዳዳሪዎችን ከተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች ሲያሳትፍ ቆይቶ በስኬት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የበርካታ ታታሪዎችና የሥራ ወዳዶች ከተማ በሆነችው ውቢቷ ሃዋሳ ከተማ ቅዳሜ ጥቅምት 30/2017 በሃይሌ ሪዞርት በተከወነ ልዩ መርሐ ግብር፤ የ2ተኛው ዙር አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ በመሆን የብር ሁለት መቶ ሺህ ተሸላሚ ለነበረው ተወዳዳሪ ባጢሶ በየነ በአቢሲንያ ባንክ ሃዋሳ ዲስትሪክት ደማቅ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል።
ደማቅ በነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት፤ የክልሉን የሥራ ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጨምሮ በርካታ የመንግሥት አመራር ተወካዮችና የአቢሲንያ አሚን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የተገኙ ሲሆን፤ የክልሉ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የመጅሊስ አመራሮችና የባንኩ ተቀዳሚ ደንበኞች እንደዚሁም ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በክብር እንግድነት በመገኘት ለአሸናፊው የእንኳን ደስ አለህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዚህ ልዩ መርሐ ግብር የክልሉ የሥራ ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊዋ ክብርት አገረፅዮን አበበ አቢሲንያ ባንክ የሥራ ፈጠራ አቅምን ለማሳደግ እየከወነ የሚገኘውን ምስጉን ተግባር በማድነቅ፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የበለጠ የሚያግዙ እንደ “አሚን አዋርድ” ዓይነት የሥራ ፈጠራ ውድድር መድረኮች መብዛታቸው ለአገር ዕድገትና ልማት ሰፊ ትርጉም እንዳለው የገለጹ ሲሆን፤ የባንኩን ተግባር “አርኣያነት ያለው” ነው በማለት አሞግሰዋል።
ንቁ፣ አምራችና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የሥራ ፈጠራ አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ያወሱት የአቢሲንያ አሚን ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ አብዱልቃድር ሪድዋን፤ በንካችን ለሁለት ዙሮች በድምቀት የከወነው “አሚን አዋርድ” የሥራ ፈጠራ ውድድር ባለራዕይ ወጣቶችን ለማብቃት እንደ ባንክ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን የምንወጣበት አንድ መንገድ ነው ሲሉ ሂደቱን በምልሰት አስታውሰዋል።
በሁለት ዙሮች በድምቀት ሲከናወን ቆይቶ ፍፃሜውን ያገኘው አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር ከተለያዩ የሃገራችን ክልሎች 135 ተወዳዳሪዎችን ሲያሳትፍ የቆየ ሲሆን፤ በቴክኖሎጂ ግብዓቶች፣ በግብርና ምርቶች ማሳደጊያ፣ በግንባታ ቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በዶመስቲክ ትሬድ፣ በሰርቪስ፣ በታዳሽ ኃይል፣ በትምህርትና ጤና እንደዚሁም በኢ ኮሜርስ ዘርፍ ተወዳዳሪዎችን በማሳተፍ ከብር ሁለት መቶ ሺህ እስከ ብር አንድ ሚሊየን ድረስ ሽልማት በማዘጋጀትና አሸናፊዎችን በመሸለም ፍጻሜውን ማግኘት ችሏል።
የዛሬው አሸናፊ የሃዋሳው ባጢሶ በየነ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ሁለተኛው ዙር አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር የተለያዩ የግብርና ተግባራትን በአንድ ላይ መፈፀም የሚችል ማሽን በመፍጠር ነበር የአምስተኛ ደረጃን በማግኘት ተሸላሚ የሆነው።
Leave a Reply