ዘመን የሚወልዳቸው አዳዲስ ግኝቶች፣ የሰውን ልጅ ውስብስብ ሕይወት በማቅለል ረገድ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ ቀላል የሚባል አይደለም። ከባዱን ሸክም ማቅለል፤ ሩቅን መንገድ ማቅረብ፤ ዳር የሆነውን ወደ መሐል ማምጣት ተችሏል። የዘመን ስጦታዎች ሰፊውን ዓለም በማጥበብ፤ ጠባቡን ሰፈር በማስፋት፤ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጥግ መቅረብ የሚቻልበትን ዕድል ፈጥረዋል።
የተፈጠሩት ዐዳዲስ የዘመን ስጦታዎች፣ በየጊዜው እየሠለጠኑ እና እየተሻሻሉ የሚመጡ በመሆናቸው ሁል ጊዜ ባሕሪያቸውን እና ጠባያቸውን በሚያስገርም ፍጥነት የሚለዋወጡ ናቸው። ትላንት አውቀነዋል፤ ለምደነዋል ያልነው ግኝት፣ ዛሬ የበለጠ እየዘመነ፤ የበለጠ እየቀረበን፤ ለአጠቃቀምም ምቹ እየሆነ ይመጣል። ታዲያ ይህንን ባሕሪውን ለመረዳት ከዘመኑ ጋር አብሮ መጓዝን ይጠይቃል።
አቢሲንያ ባንክ የባንክ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቱን በማዘመን ጊዜው ከደረሰበት ሥልጣኔ ጋር አብሮ እኩል የሚጓዝ ባንክ ነው። ይህንንም እሴት በመገንባት ለተገልጋዮቹ ምቾት የሚሰጡ እና በአገልግሎት አሰጣጡ የሚረኩባቸውን አዳዲስ የአገልግሎት አሰጣጥ መንገዶች እያስለመደ ይገኛል።
እነሆ ዛሬ! በዲጂታላይዜሽን ሥርዐት የወረቀት ንክኪን ታሪክ ያደረገ፤ በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ትልቁን ባንክ የምንቆጣጠርበትን ዕድል ያመቻቸው፤ እክሎችን በማስቀረት በተቀላጠፈ መንገድ አስተማማኝ የገንዘብ ዝውውር እንዲኖር፤ የተጣራ መረጃዎቹንም ካለምንም መንገላታት በቀላሉ እንድናገኝ የሚያስችለንን ሞባይል ባንኪንግ ልናወጋቹ ወደድን።
ብዙ ሰዎች በማንኛውም ጊዜ ከእጃቸው የማይለየው እና በየትኛው ቦታ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ስልክ ነው። ከስልክ ቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ተይይዞ የተከሠተው የሞባይል ባንኪንግ፤ በአሁኑ ጊዜ በባንክ ቴክኖሎጂ በጣም ተመራጭ ከሆኑ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ እየሆነ መጥቷል። የተለያዩ የባንክ አገልግሎት ጥያቄዎችን በፍጥነት በመመለስ ያልተፈለጉ እንግልቶችን ለማስወገድ እና ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያዎችን በመቀነስ ጊዜን ከእጅግ በላይ ይቀንሳል፡፡
የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያን በመጠቀም ቀሪ ሒሳብዎን ማረጋገጥ፤ ግብይቶችን በማንኛውም ቦታ መፈጸም፤ የፋይናንስ ሒደቶችን ጤነኛ ማድረግና ማሻሻል ያስችላል፡፡ እነዚህን አገልግሎቶች በስልክ ቀፎ ማግኘት የሚቻል ከሆነ ደግሞ ዛሬ ላይ የሞባይል ባንኪንግን መጠቀም ግድ ይላል፡፡ምክንያቱም፡-
- ገንዘብዎን በሚያንቀሳቅሱበት ሒደት ጊዜዎትን መቆጣጠር ያስችላል፤
የሞባይል ባንኪንግ ከሚሰጣቸው ቁልፍ ጥቅሞች አንዱ፣ በማንኛውም ቦታ ሆነው ሒሳብዎን እንደልብ መጠቀም ማስቻሉ ነው፡፡ ስለዚህ የሥራ ሰዓት፣ ወይም የወሩ መጨረሻ፣ አልያም የዓመቱን በጀት መዝጊያ ወቅት ሳይጠብቁ “በዕረፍት ጊዜያችሁ ብትሆኑም እንኳን” ገቢና ወጪዎን በመቆጣጣር ቀሪ ሒሳብዎን (Balance) እንዲያውቁት ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ ጊዜንና ገንዘብን ከመቆጠብ በላይ ነው፡፡
- ገንዘብ በፈጣን በማስላለተፍ መጨናነቆችን ያስወግዳል፤
ምናልባት ክፍያን አሁን መፈጸም ያስፈልግዎት ይሆናል፤ በሥራ ጫና ሳይከውኑ እረሱት እንበል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ግዴታ ባንክ ወይም ኤቲኤም ማሽን ወዳለበት መሄድ ግድ ይልዎታል፡፡ ይኽ ደግሞ በፍጥነት የሚሆን አይደለም፡፡ ስለዚህ ባሉቡት ሆነው ወዲያውኑ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ የሚያስችሎት መላ ማግኘት አለብዎ፡፡ ሞባይል ባንኪንግ ሌላው ቁልፍ ጠቀሜታ ይህ ነው፡ የገንዘብ የማስላለተፍ ሒደቶችን ወዲያውኑ እንዲከወኑ ይፈቅዳል፡፡ የዚህን ያህል ቀላል ነው።
- በመጨረሻ ደቂቃ የተፈጸሙትን ዝውውሮች በቀላሉ ማወቅ ያስችልዎታል፤
ሞባይል ባንኪንግ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ምን ምን ዐይነት ክፍያዎችን ለመፈጸም ማቀድ እንዳለብዎ ያግዝዎታል። ተደጋጋሚ ክፍያዎችን በቀላሉ ለማቀናበር፤ ከቁጠባዎ ገንዘብ ወደ ቼክ አካውንት ለማስገባት፤ እንዲሁም ማስተላለፎችን ቀላል በማድረግ በየቅጽበቱ መረጃን ያቀብልዎታል።
- ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በምቾት ለመከታተል ይረዳል፤
ቀሪ ሒሳቦችን ለመፈተሽ፤ ፈንዶችን ለማስተላለፍ፤ በየዕለቱ በሚደረጉ ግብይቶች ሊኖር የሚችልን ማጭበርበር ለመከላከል ይረዳል።
- ጥሩ በጀት ለማውጣት ያግዛል፤
በእጅዎ የሚገኘውን ገንዘብ ከማውጣትዎ በፊት ያለዎትን ቀሪ ሒሳብ በማረጋገጥ ገቢና ወጪዎን እንዲያመጣጥኑ ያስችላል፤ አስተማማኝ በሆነ መንገድ ግቦችን ለማሳካት በዕቅድ እንዲመሩ ይረዳዎታል፡፡
ሞባይል ባኪንግ ገንዘብዎን በቀላሉ ማስተዳደር የሚችሉበት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ቢሆንም፤ በዚያ ልክ ደግሞ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም የሞባይል መተግበሪያ የተቀየሰው የተጠቃሚውን ወይም የተገልጋዩን ዐቅም እና የሚወስደውን ኃላፊነት ግምት ውስጥ በማስገባት ስለሆነ፤ ከአገልግሎቱ ጋር ደኅንነቱም በራሱ በባለቤቱ እጅ መሆኑን መረዳት ስለሚፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ ሊወስዷቸው የሚገቧቸውን ተጨማሪ እርምጃዎች እና የደኅንነት ምክሮች ከዚህ በታች አቅርበንልዎታል፡-
- ስልክዎን ይቆልፉ፡
ጠንካራ የይለፍ ቃላትን፣ ፓተርን፣ የፊት ወይም የጣት አሻራ በመጠቀም ስልክዎን ይቆልፉ። ምናልባት ስልክዎ በተሳሳተ እጅ ላይ ቢወድቅ መረጃዎች እና መተግበሪያዎች በቀላሉ ሊደረስባቸው አይችሉም፡፡ ስለዚህ ረዥም ቃላትን፣ ፊደላትን እና ቁጥሮችን በማጣመር፣ ያልተለመዱ ሐረጎችን ወይም ቅርጾን በመጠቀም ጠንካራ የይለፍ ኮድን መፍጠር ይችላሉ። በመሆኑም በየሶስት/3/ወሩ የይለፍ ኮዶችን መቀየር አይርሱ።
- ክፍት የሆነ ዋይፋይ አይጠቀሙ፡-
ነጻ ዋይፋይ ባለበት የሚጠቀሙ ከሆነ ጥንቃቄ ያድርጉ። ኦን ላይን የባንኪንግ አገልግሎቶችን ለመጠቀም አይሞክሩ። ምክንያቱም ማንኛውም አካል ሰብሮ እንዲገባና መረጃዎን በቀላሉ እንዲያገኝ ያስችሉታል። ስለዚህ የመስመር ላይ ግዢዎችን አለመፈጸም፤ ሒሳቦችን ላለመክፈል መጣር ይኖርብዎታል። ነገር ግን ክፍያዎችን ለመፈጸም ሕዝባዊ ዋይፋይ መጠቀም ግድ ከሆነ ቨርቹዋል የግል አውታሮችን (VPN) መጠቀም እንዳለብዎ አይርሱ፡፡
- መተግበሪያዎች ማሻሻል (Update) አይርሱ፡-
ባንኮች ለሚያዘጋጇቸው መተግበሪያዎች አዳዲስ ባሕሪያትን ለማስተዋወቅ እና የመተግበሪያውን ደኅንነት ለመጠበቅ ማሻሻያዎችን በየጊዜው ይለቃሉ። ስለዚህ መተግበሪያዎችን በየጊዜው በማዘመን ወዲያውኑ መጫን ይጠበቅቦታል ማለት ነው። ይህንን በማድረግ አስተማማኝ የሆነ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎችን መጠቀም ይችላሉ፡፡
- ከአሳሳች መልእክቶች ይጠበቁ
ባንኩ ከሚልክልዎት የይለፍ መለያዎች፣ ቁጥር ወይም ምሥጢራዊ መረጃዎች ውጪ ከሌሎች አስመስለው ከሚላክልዎ መልእክቶች ከምን ጊዜውም በላይ ይጠበቁ፡፡
የአቢሲንያ የሞባይል ባንኪንግ መተግበርያ ከፕሌይ ወይም አፕል ስቶር በማውረድ ካሉበት ቦታ ሆነው ባንኩ የሚሰጠውን አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡ ዘመኑን በመረዳት የዘመኑ ውጤቶችን መጠቀም ወደ ፊት ለመራመድ ያስችላል፡፡
አቢሲንያ የሁሉም ምጫ!!
ምኒልክ ብርሃኑ
Leave a Reply