አሁን ላይ በአገራችን ካርዶችን ለግዢ፣ ለወጪ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ለኦንላይን ክፍያ መጠቀም ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የካርዶቹም ዓይነት እየጨመረ እንዲሁም የብሔራዊ ባንክ ፈቃድን ተከትሎ ካርዶቹን የመስጠትም ሥራ ከባንኮች በተጨማሪ በሌሎች አካላት ወይም ድርጅቶች ጭምር እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ሆኖም ብዙ ሰዎች በክሬዲት ፣ ዴቢት እና ቅድመ ክፍያ ካርዶች መካከል ያለው መመሳሰልና ልዩነት በግልፅ አይታያቸውም፡፡፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት ግልፅ ነው፡፡ እነዚህ ካርዶች ብዙ የሚያመሳስላችው ነገሮች (አገልግሎቱ የሚያበቃበት ቀን፣ የካርድ መለያ ቁጥሩ PAN፣ ሥም፣ የካርድ ሰጪውና የቪዛ ወይም ማስተር ካርድ መለያዎች አንዲሁም አሁን ላይ በተወሰኑት ላይ የኮንታክትለስ ምልክት) በካርዶቹ ላይ በተመሳሳይ መልኩ በመኖራቸው ምክንያት ሲሆን፣ ካርዶቹ ግን መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው ናቸው፡፡
የካርዶቹን ተፈጥሮአዊ ልዩነት እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከት፡-
ቅድመ ክፍያ ካርድ
የቅድመ ክፍያ ካርድ የባንክ ሒሳብ መኖር ሳያስፈልግ ወይም ከባንክ ሒሳብ ጋር ሳይገናኝ በዲጂታል ክፍያ ዋሌት (Digital Payment Wallet) አማካኝነት በካርድ ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል ነው፡፡
እነዚህ ካርዶች አብዛኛውን ጊዜ በቪዛ ወይም ማስተር ካርድ የሚደገፉ በመሆናቸው ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ወይም በውጭ አገርም ሊሠሩ የሚችሉ ናቸው፡፡
የቅድመ ክፍያ ካርዶች አንድ ልዩ የሚያደርጋቸው በገንዘብ ወይም በክፍያ መጠን ላይ ገደብ ያላቸው መሆኑ ሲሆን፣ በካርዶቹ ላይ ያለው ገንዘብ ካለቀ በኋላ እንደገና እስኪጫንባቸው ድረስ መጠቀም አይቻልም፡፡
ለተለያዩ ዓላማ የሚውሉ የቅድመ ክፍያ ካርድ አይነቶች ያሉ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡
1-የቅድመ ክፍያ የሥጦታ ካርዶች
እነዚህ ካርዶች በሥጦታ መልክ ከተለያዩ አካላት ሊገኙ የሚችሉ ሲሆን፣ ካርዶቹ የያዙት የገንዘብ መጠን ካለቀ በኋላ ካርዶቹን መልሶ መጠቀም አይቻልም፡፡
2-የችርቻሮ ቅድመ ክፍያ ካርዶች/Retail Prepaid Cards
እነዚህ ካርዶች ከሥጦታ ካርዶች የተለዩ ሲሆኑ፣ ነዳጅ አቅራቢዎች፣ አየር መንገድ ወይም ሱፐር ማርኬቶች ከባንክ ጋር ወይም ከካርድ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተጠቃሚዎች ክፍያ ወይም ግብይት በሚፈፅሙበት ወቅት የሽልማት ነጥቦችን ፣ የአየር ማይሎችን (Miles)፣ ቅናሾችን፣ ለመስጠት የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
3-የቅድመ ክፍያ የጉዞ ካርዶች
የቅድመ ክፍያ የጉዞ ካርዶች ወደ ውጭ ጉዞ ለሚያደርጉ ግለሰቦች፣ ትኬትና ቪዛ እንዲሁም የደንበኝነት ሁኔታ ታይቶ በባንኮች የሚሰጡ ሲሆኑ፣ የገንዘቡ መጠን በውጭ ምንዛሬ ተጭኖ በሄዱበት አገር ሆስፒታሎች፣ ሱቆች እንዲሁም ለኦንላይን ክፍያዎች ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡
በካርዶቹ ላይ የተጫነው ገንዘብ ሲያልቅና ተጨማሪ ገንዘብ ከተፈለገ እንደገና መሙላት ይጠይቃል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ ካርዶች ፓን ቁጥርን በመጠቀም የተወሰነ ገንዘብ ሊተላለፍባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡ የአቢሲንያ ባንክ የጉዞ ቅድመ ክፍያ ካርዶች ከተጫነባቸው የመጀመሪያ የገንዘብ መጠን በላይ አስከ 3000 የአሜሪካን ዶላር ድረስ ከሌላ አካል ሊቀበሉ ወይም ሊተላለፍባቸው ይችላል፡፡
4-ለጠቅላላ አገልግሎት የሚያገለግሉ የክፍያና ግዢ ካርዶች
እነዚህ ካርዶች ለማንኛውም ዓይነት የዕለት ተዕለት ግዢና ክፍያዎች የሚያገለግሉ ሲሆን፣ የተጫነባቸው ገንዘብ ሲያልቅ እንደገና እየተሞሉ(Reloadable) ጥቅም ላይ የሚዉሉ ናቸው፡፡ የቅድመ ክፍያ ካርዶች ፣ ወጪዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆኑ ከሌሎች የተለየ ጠቄሜታ አላቸው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በካርዶቹ ላይ የተቀመጠው ገንዘብ መጠን አንድ ጊዜ ወጪ ከተደረገና ካለቀ፣ አለቀ ማለት ነው፡፡ ጥናቶችም እንደሚሳዩት ብዙ ሰዎች ከጥሬ ገንዘብ ይልቅ በካርዶች ከመጠን በላይ ማውጣት ይቀላቸዋልና፡፡
ዴቢት ካርድ
ዴቢት ካርዶች በአብዛኛው ከተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጋር ግንኙ(Link) ሆነው የሚሠሩ ናቸው፡፡ በዚህም በቁጠባ ወይም በተንቀሳቃሽ ሒሳብ ውስጥ የሚኖረውን የገንዘብ መጠን ያህል ወጪ ማድረግ፣ ግብይቶችን ማካሄድ ወይም ክፍያዎችን መፈፀም ያስችላሉ፡፡ በሌላ አገላለፅ በሒሳብ ውስጥ የሚገኘውን ገንዘብ በካርዶቹ አማካኝነት በቀላሉ ለተፈለገው አላማ መጠቀም ማስቻላቸው ነው፡፡
አሁን ላይ በዴቢት ካርድ ከአቅም በላይ ወይም በሒሳብ ከሚገኘው ገንዘብ መጠን በላይ ማውጣት ከአለመቻሉ ባለፈ፣ ተጨማሪ ወጪ ማድረግ ቢፈለግ እንኳን ተጨማሪ የወጪ ወይም የክፍያ ገንዘብ ማግኘት አይቻልም፡፡ በርግጥ፣ አሁን ላይ አገልግሎቱ ጥቅም ላይ አልዋለም እንጂ፣ አንዳንድ የዴቢት ካርዶች ከኦቨር ድራፍት ፋሲሊቲ ጋር ግንኙ ሆነው ሊሠሩ የሚችሉበትም ሁኔታ ይኖራል፣ ይህ ሲሆን ሒሳብ ውስጥ ከሚገኘው ገንዘብ መጠን በላይ ለመጠቀም ይቻላል፡፡
ክሬዲት ካርድ
ክሬዲት ካርድ በአጭሩ ለግብይት፣ ለሌሎች ክፍያዎች ወይም ወጪዎች የሚሆን ገንዘብን በብድር መልክ ማግኘት የሚቻልበት ሲሆን፣ በካርዱ ለመጠቀም የተፈቀደው የብድር መጠን ወይም የብድር ገደብ ድረስ መገልገል ያስችላል፡፡
የብድር መጠኑን ለማሳደግ፣ ጥሩ የብድር አጠቃቀም ወይም ክሬዲት ካርድን በኃላፊነት በመጠቀም የብድር ደረጃን (Credit Score) ማሻሻል ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክሬዲት ካርድን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ መጠቀም ከልክ በላይ ወጪ ማውጣትን ፣ የብድር መከማቸትን ፣ የብድር ክፍያ መዘግየትን ብሎም የብድር መበላሸትን ሊያሰከትል ይችላል፡፡
በመጨረሻም ከካርዶች ጋር በተገናኘ፣ በተለያዩ አገልግሎት በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ምድቦች በፕርሚየም፣ ፕላቲንየም፣ ጎልድ ወይም መደበኛ መልኩ የተለያዩ ጥቅሞች ያሏቸው ሲሆን፣ የጥቅሞቹ አይነት፣ መጠንና የአገልግሎት ክፍያቸው እንደ ካርድ ሰጪው ባንክ ወይም ድርጅት የሚወሰንና የሚለያይ ነው፡፡
በአለማየሁ ስሜነህ
Leave a Reply