ብዙ ጊዜ ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮች ንግድ ላይ ያጋጥማሉ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከቁጥጥር በላይ በሆኑ፣ በውጫዊ ኹነቶች ምክንያት በንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖዎች ይፈጠራሉ። ግን ልክ እንዲዚህ ዐይነት ችግር ቢገጥምዎትስ? በቤትዎ ሽንቁር ጠብ እያለ የሚገባው ፍሳሽ፣ ከእግርዎ በታች ቀስ በቀስ እየሞላ ውኃው ጭንቅላትዎ ላይ ቢደርስስ? በተለይ ዋና የማይችሉ ከኾነ! ነገሩ አለቀ። ለበርካታ ዓመታት የደከሙበት ንግድ መፍትሔ በቶሎ ሳያበጁለት ቀስ እያለ ከማይወጡት ቅርቃር ውስጥ ቢከትዎስ? ወይም ባለህበት እርገጥ እየሆነ እድገትዎ ዘገምተኛ ቢሆንስ ምን ያደርጋሉ?…. ለእነዚህ ጥያቄዎች ወሳኝ ሆነው መልስ ማግኘት ቀላል አይደለም።
ለንግድ እንቅስቃሴዎ ወሳኝ የኾነ ትልቅ ጉዳይ አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ጤነኛ የገንዘብ ፍሰት (Positive Cash Flow) መፍጠር። በአንድ የንግድ ተቋም ላይ የሚደረግ የገንዘብ እንቅስቃሴ የገንዘብ ፍሰት እንለዋለን። የገንዘብ ፍሰት በተቋሙ ውስጥ ወደ ውስጥና ወደ ውጪ የሚተላለፈውን የተጣራ ጥሬ የገንዘብ መጠንን ያመለክታል:: ከምርቶች ሽያጭ፣ ከወለድ፣ ከኢንቨስትመንት ወዘተ. የሚገኙትን ገንዘብ እንደ ገቢ ሲታይ እና በዚህ መንገድ የተገኘው ገንዘብ ደግሞ ለተለያዩ ወጪዎች ይውላል። በዚህ ሒደት ውስጥ ጤነኛ ወይም አዎንታዊ የገንዘብ ፍሰት አለ የምንለው፣ የተቋሙ ገቢ እየጨመረ በመምጣቱ እና ተቋሙ ያለበትን ግዴታዎች (ብድር፣ ደሞዝ፣ የቤት ኪራይ፣ ለባለ አክስዮኖች የሚከፍል፣ ተጨማሪ ኢንቨስት የሚያደርግ ከሆነ) ሲወጣ ነው። አንድ ድርጅት ጠንካራ አቋም ላይ እንዳለ የሚረጋገጠው አዎንታዊ የገንዘብ ፍሰትን በማመንጨት እና የረጅም ጊዜ ነጻ የገንዘብ ፍሰትን (Free Cash Flow) ከፍ ለማድረግ ባለው ችሎታ ነው።
የንግድ ድርጅት ባለቤት ከሆኑ እና በከፍተኛ ፍጥነት ሽያጭዎ እያደገ ትርፋማ ካደረግዎ በእርግጠኝነት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እየሄዱ ነው። ምንም እንኳን ትርፋማ ቢሆኑም፣ የፋይናንስ ሥርዐቶችን በብቃት እየመሩ ካልሆነ በገንዘብ ፍሰት ችግር ሊመቱ ይችላል። ስለዚህ በንግድ ውስጥ ጤናማ የገንዘብ ፍሰት ለመፍጠር ገቢን ማሳደግ እና ወጪዎችን መቀነስ ከአስፈላጊነት በላይ ነው።
ያለብዎት ዕዳዎች በጊዜው ካልተከፈሉ፣ የሽያጭ ገንዘብ በወቅቱ ካልሰበሰቡት የገንዘብ ፍሰት ችግሮች ያጋጥምዎታል። ይህ ደግሞ፣ ንግድዎ ላይ ወደ ኋላ በመጎተት እክል ሊፈጥርብዎ ይችላል፤ የደመወዝ፣ የሕንጻ ክራይን ወዘተ ክፍያን በወቅቱ እንዳይፈጽሙ ያደርግዎታል።
የገንዘብ ፍሰትን ማሻሻል የሚከተሉት ስልቶች ተግባራዊ ያድርጉ፤
- በቅድሚያ የገንዘብ ፍሰት በጀት ያዘጋጁ፤
በጀት ወጪና ገቢያችን የምናመጣጥንበት ስልት ነው፤ የገንዘብ ፍሰት በጀት ደግሞ ወቅታዊ የገንዘብ ፍሰቶችን የሚያንፀባርቅ በመሆኑ የትርፍ እና ኪሳራ ሒደቶችን እንድናውቅ፤ በሒሳባችን ምን ምን ዐይነት የገንዘብ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንዳለ፤ ወደፊት አዳዲስ እቅዶችን በማቀድ ምርጥ አጋጣሚዎችን መጠቀም እንድንችል እና አደጋዎችን እንድንለይ ያስችለናል። ስለዚህ የሚመጣውን እና የሚወጣውን ገንዘብ በማመጣጠን በበጀት መንቀሳቀሱ የገንዘባችን ፍሰት ጤናማና አዎንታዊ ያደርገዋል ማለት ነው።
2. ቁጠባን ባህል ያድርጉ፤
ብዙ ጊዜ አዳዲስ የንግድ ሥራችን ለመጀመር ገንዘብዎን በሙሉ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ይኽ ደግሞ ትልቅ አደጋ ውስጥ ሊከትዎ ይችላል። ስለዚህ ቁጠባን ባህል በማድረግ ከገቢዎ ትንሽ ገንዘብ ማስቀመጥን ይለማመዱ። ከዛም በቆጠቡት ገንዘብ አዲሱ ሥራ ላይ ኢንቨስት ያድርጉ። ለረጅም ጊዜ ፕሮጀክቶ የሚሆን የረጅም ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብ በማግኘት የገንዘብ ፍሰትን ማመጣጠን ይችላሉ።
3. የመሸጫ ዋጋን ከፍ ያድርጉ፤
አዎንታዊ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖር ከሚያደርጉት ምርጥ መንገዶች አንዱ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘት ነው። ስለዚህ በጥቂት ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪን በማድረግ ገቢዎን ማሳደግ ይገባዎታል። ምናልባት ደንበኞችን ስለማጣት የሚያሳስብዎት ከሆነ፣ ለአዳዲስ ደንበኞች አዲስ ዋጋ ማውጣት እና የቆዩ ደንበኞችን በመጀመሪያው ደረጃ ማቆየት ይችላሉ። በአማራጭ፣ በጥቂት ምርቶች ላይ ወይም ለጥቂት ነባር ደንበኞች ላይ ብቻ የዋጋ ጭማሪን በማድረግ የገቢ ፍሰት መጨመር ይችላሉ።
4. ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ሥርዐቶችን መተግበር፤
ምርታማነትን ማሻሻል ወደ አዎንታዊ የገንዘብ ፍሰት ለመድረስ ያችላል። ካላችሁ ሠራተኞች ጋር ንግድዎን ማቀላጠፍ እስከቻሉ ድረስ ተጨማሪ ሥራዎችን ማከናወን አያቅቶትዎትምና፤ አዳዲስ ስልቶችን በመከተልና ዘመናዊ (ወቅታዊ) አሠራሮችን በመተግበር ንግድዎን ከፍ ማድረግ ላይ ያተኩሩ።
5. ወጪዎችን ይቀንሱ፤ ገቢን ይጨምሩ፤
የገንዘብ ፍሰትዎን ለማሻሻል ቀጥተኛ ከሆኑ መንገዶች አንዱ ብዙ ገንዘብ ማግኘት እና ትንሽ ገንዘብ ማውጣት ነው። ይህንን ለማድረግ ዋጋዎች መጨመር፣ አዳዲስ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ማቅረብ፣ ምርቶችን ለማዳረስ ማስታወቂያዎችን መጠቀም፤ የፍጆታ ወጪዎችን በመቀነስ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ መሣሪያዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ፤ ንብረትዎንና የሥራ ቦታዎን ከንግዱ ጋር በማጣጣም በትንሹ መጀመር እና መገንባት በብዙ መልኩ ተመራጭ መንገዶች ናቸው።
6. ብድርን ቶሎ በመክፈል የወለድ ወጪን መቀነስ፤
ብድርን በፍጥነት መክፈልና ብድርን መዝጋት፤ የገንዘብ ፍሰትን ጤነኛ ከማድረግ ባለፈ ነጋዴዎች የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዐት እንዲኖራቸው፣ ገቢና ወጪን አጣጥመው ትርፋቸውን እንዲያሳድጉና ከፍ ያለ ገቢ እንዲኖራቸው ያስችላል።
7. የቅድመ ክፍያ አገልግሎቶችን ይስጡ፤
በቀደመው የውል ስምምነት መሠረት ምርቶችን ወይም አገልግሎቶችን በዱቤ ሊያቀርቡ ይችላሉ። ይኽ ደግሞ ወደ እርስዎ የሚመጣውን የገንዘብ ፍሰት ያዛባዋል። ከተለመደው አሠራር ወጥተው፣ ለደንበኞች በቅናሽ ደረሰኝ ምርቶችን በማቅረብ ቀደም ብለው እንዲከፍሉ ልታሳምኑ ትችላላችሁ። ይህን አነስተኛ ገንዘብ እንዲቀበሉ ቢያደርግም፣ በቶሎ ገንዘቡ ስለሚመጣ አዎንታዊ የገንዘብ ፍሰት እንዲፈጥሩ ይረዳዎታል።
እነዚህ ጥቂት ስልቶችን በመጠቀም ንግድዎን ከገንዘብ ቀውስ ውስጥ ማውጣት ይችላሉ። አሁን በሽንቁሩ ጠብ እያለ የሚፈሰውን ውኃ ማስቆም ወይም ማስተካከል አያቅትዎትም።
አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!
ምኒልክ ብርሃኑ!
Leave a Reply