ትላንት የባንክ አገልግሎት ጊዜ የሚወስድ ነበር። ዛሬ፣ ብዙ አማራጮች አሉን፤ አንደኛው የሞባይል ባንኪንግ ነው፡፡ ታዲያ የሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው?
አዎ! የሞባይል ባንኪንግ ደኅንነቱ የተጠበቀ ብቻ ሳይሆን በጣም ምቹና ፈጣን፤ በየቅርንጫፎች በመሔድ የሚመጣውን መስተጓጎልን የሚያስወግድ፤ በቀላሉ ገንዘብዎን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የሚመች መንገድ ነው።
የሞባይል ባንኪንግ የተለያዩ የባንክ መተግበሪያዎችና ዘዴዎች በመኖራቸው ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው። መተግበሪያን በሚጠቀሙበት ጊዜ የመረጃዎን ደኅንነት ለመጠበቅ እንዲረዳዎ እነዚህን ምክሮች ዘወትር ተግባራዊ ያድርጉ።
- የይለፍ ቃልዎን የግልዎ ያድርጉት፤
ብዙ ጊዜ እርስዎ ከሚገለገሉበት ባንክ የደወሉ በማስመሰል ወይም መልእክት በመላክ የግል መረጃና የይለፍ ቃልዎን በቀጥታ በቀጥታ የሚጠይቁዎት አጭበርባሪዎች ይኖራሉ። የፋይናንስ ተቋማት የሞባይል መለያ ይለፍ ቃል ወይም ሌላ ምሥጢራዊ መረጃ የሚጠይቅ መልእክት አይልኩም። ስለዚህ ለእንደዚህ ዐይነት መልእክት እርስዎ በፍጹም መልስ አይስጡ።
- ሕዝባዊ ዋይ ፋይን አይጠቀሙ፤
ሕዝባዊ ዋይ ፋይ ያላቸው ቦታዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ አይደለም፤ ለጠለፋ ተጋላጭ ናቸው። ወደ መለያዎ ከመግባትዎ በፊት፣ ከሕዝብ አውታረ መረብ ጋር አለመገናኘትዎን ያረጋግጡ። ከዚያ ይልቅ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ኔትወርክ መጠቀም ጥሩ መፍትሔ ነው። እንዲሁም የባንክ መተግበሪያዎችን በእነዚህ ቦታዎች አያውርዱ፡፡
- ኦፊሻል የባንክ መተግበሪያን ይጠቀሙ ፤
ባንኮች ኦፊሻል መተግበሪያዎችን ያቀርባሉ። እነዚህ መተግበሪያዎች በSMS ወይም በE-mail መረጃን ከመላክ የበለጠ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ነው። መተግበሪያውን ከማውረድዎና ከመጫንዎ በፊት የባንኩ መተግበሪያ መሆኑን ያረጋግጡ። አገልግሎቶችን ከጎግል ላይ በቀጥታ እያሰሱ ከመጠቀም ይልቅ፤ የፋይናንስ ተቋምዎን መተግበሪያዎች መጠቀም በበለጠ ደኅንነቱ የተጠበቀ ይሆናል።
- ተጨማሪ የደኅንነት መሳሪያዎችን ያውርዱ፤
የፋይናንሺያል መረጃዎች በጣም አስፈላጊ ስለሆኑ መረጃዎችን ለመጠበቅና ከማናቸውም መሰናክሎች ለመጠበቅ የደኅንነት መሳሪያዎችን እንደ VPN ዐይነት መጫን አይርሱ።
- መተግበሪያዎቹን እያዘመኑ ያቆዩ፤
እየተገለገሉበት ያለው መተግበሪያ በቅርብ ጊዜ የዘመነ መሆኑን ያረጋግጡ። መተግበሪያዎች በየጊዜው ደኅንነትን የሚያሻሽሉ ክፍሎችን ስለሚይዙ በቀላሉ እንዳይጠለፉ ያደርጋሉ።
- ከተጠቀሙ በኋላ ዘግተው መውጣትዎን ያረጋግጡ፤
አንዴ መተግበሪያ ተጠቅመው ከጨረሱ በኋላ ዘግተው ይውጡ። ይህን ሲያደርጉ አንደኛ ግንኙነቱ ይቋረጣል፤ ሁለተኛ ምናልባት ስልክዎ ወይም መሣርያዎ ከጠፋ አደጋ ላይ አይጥልዎትም።
- መተግበሪያዎችንና መረጃዎችን ይሰርዙ፤
ስልክዎን የሚቀይሩ ወይንም ለሌላ ሰው የሚሰጡ ከሆነ መረጃዎችንና መተግበሪያዎችን መሰረዝዎን ያረጋግጡ። ስልክዎን ከመጣልዎ ወይም ከመሸጥዎ በፊት የግል መረጃን የያዙ ጽሑፎችንና ኢሜሎችን ይሰርዙ።
- ስልክዎ ከጠፋብዎ – የፋይናንስ ተቋምዎን ያነጋግሩ፤
በተቻለ አቅም ተንቀሳቃሽ ስልክዎ እንዳይጠፋ ይጠንቀቁ፡፡ምናልባትም ስልክዎ ቢጠፋ የፋይናንስ ተቋሙን ማነጋገር አይርሱ፡፡ ምክንያቱም ስልኩ በሌላ ሰው እጅ ከገባ የሞባይል ባንኪንግ እንዳይጠቀም ቀድመው ማሳገድ ይችላሉና።
- ሊንኮችን አትከተሉ
በጽሑፍ ወይም በኢሜል የተላከን የባንክ ሊንክ በፍጹም መከተል የለባችሁም። እነዚህ አገናኞች ወደ ተበላሸ ድረ-ገጽ ሊመሩዎት ይችላሉ። ይህን ካደረጉ መረጃዎትን ለአጭበርባሪዎች አሳልፈው የሚሰጡበት እድል ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ሊንኮችን ከመክፈት በመቆጠብ በቀጥታ ወደ ድረ ገጽ መሔድ ይመረጣል።
አቢሲንያ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ደኅንነታቸው የተጠበቁ፣ ከዘመኑ ጋር አብረው የሚዘምኑ፣ ቀልጣፋና በጣም ምቹ ናቸው፡፡ አገልግሎቶቹን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን እንዴት መጠቀምና ደህንነቱን መጠበቅ እንዳለብዎ ከበቂ መረጃ ጋር ማቅረቡ መለያው ነው፡፡
አቢሲንያ የሁሉም ምርጫ!
ምኒልክ ብርሃኑ
Leave a Reply