አቢሲንያ ባንክ ከወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ Wegen Technology Solutions ጋር በመተባበር ወደ አገር ወስጥ ገንዘብ ማስተላለፍን ለማቀላጠፍ የተዘጋጀውን “Wegensend” የተባለውን ድረ-ገፅ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል። ይህ ፈጠራ የተሞላበት ድረ-ገፅ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ለመደገፍ ገንዘብ የሚልኩበትን መንገድ ያለምንም ክፍያ፣ አስተማማኝ እና ምቹ በሆነ መልኩ በማዘጋጀት የቀረበ ነው። በቅርቡም ድረ-ገጹ በመተግበሪያ(APP) በአንድሮይድና አይኦኤስ ይቀርባል ፣ ይህም በተለያዩ አማራጮች በመገኘት ለብዙ ተጠቃሚዎች ተደራሽነትን ያረጋግጣል።
ገንዘብ የተላከላቸው ደንበኞች ገንዘባቸውን በአቢሲንያ ባንክ ሒሳባቸው እንዲሁም በጥሬ ገንዘብ መቀበል የሚችሉባቸው አማራጮች ተመቻችተውላቸዋል።
የሀገራችንን ገንዘብ ዝውውር መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት እና የዳያስፖራው ማህበረሰብ በብዛት ሊጠቀምባቸው የሚችላቸውን አገሮች በመለየት ካናዳ፣ እስራኤል፣ ጣሊያን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስዊድን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ (አሜሪካ) በወገን ሴንድ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ የሚላክባቸው አገሮች ናቸው። ወደፊትም ብዙ አገሮችን ለመሸፈን እየተሠራ ሲሆን፣ አሁን ባለው የሥራ ፈቃድ ተጠቃሚዎች በአንድ ወር እስከ አምስት የሚደርሱ ግብይቶችን በማድረግ ለጓደኞቻቸው ወይም ለቤተሰባቸው በወር ውስጥ እስከ 1000 ዶላር መላክ ይችላሉ።
የአገልግሎት ክፍያው ነጻ መሆኑ ወገን ሴንድን ከአብዛኞቹ የገንዘብ ማስተላለፊያ መንገዶች የተለየ ያደርገዋል፡፡ ይህም ከሚላከው ገንዘብ ላይ በአማካኝ እስከ 6 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ከሚጠየቅበት ከዚሁ ዘርፍ ጋር ሲነጻጸር ደንበኞች በWegensend በነፃ መገልገል መቻላቸው እንደ ትልቅ ጥቅም የሚታይ ነው።
መተግበሪያው በቅርቡ ሊያካትታቸው ካሰባቸው አገልግሎቶች አንዱ ተጠቃሚዎች ውጭ አገር ያለን ሰው ገንዘብ እንዲልክላቸው መጠየቅ ሲፈልጉ «ገንዘብ ላክልኝ» ብለው የሚጠይቁበት አሰራር ለአብነት የሚጠቀስ ነው።
ይህ አዲሱ ድረ-ገፅ አቢሲኒያ ባንክ ለውድ የዲያስፖራ ደንበኞቹ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ተጠቃሚዎች የፋይናንስ አገልግሎትን ለማዘመን የሚያደርገውን ጥረት እንዲያጠናክር ያስችለዋል።
ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ፣ ከዚህ ቀደም ወገን ፈንድን (Wegenfund) ከአቢሲንያ ባንክ ጋር በመተባበር መጀመሩ ይታወቃል፡;፡ በዚህ አገልግሎቱም የበጎ አድራጎት ተግባራትን እና የግል የገንዘብ ማሰባሰብያ ጥረቶችን በማቀላጠፍ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ በአቢሲንያ ባንክና በወገን ቴክኖሎጂ ሶሎሽንስ መካከል ያለው አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማዘመን ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ።
ስለ ወገን ሴንድ (Wegensend) የበለጠ ለማወቅ ፡ [www.wegensend.com] [ድረ-ገጽን] ይጎብኙ።
Leave a Reply