ባንካችን አቢሲንያ በዋናው መስሪያ ቤት በሚገኘውና ከጫካ ቡና ጋር በመተባበር የከፈተውን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በካፌ የሚሰጠውን ማዕከል በትላንትናው ዕለት ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም የባንካችን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ የጫካ ቡና ባለቤት አቶ ብስራት በላይ እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አስመርቋል፡፡
አቢሲንያ ባንክ ሁሌም ቢሆን ዘመናዊ የሆኑ የባንክ አገልግሎቶችን በማቅረብ ፈር ቀዳጅና በሁሉም ደንበኞች ዘንድ ተመራጭ ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ባንኩ ከ930 በላይ ቅርንጫፎች ሲኖሩት ከ1600 በላይ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች ((ኤ.ቲ.ኤሞችና) ከ3000 በላይ የሽያጭ ማሽኖች (ፖሶች) እንዲሁም ዘመናዊ የሞባይልና የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎቶችን በስራ ለይ አውሏል፡፡
በሌላ በኩል ባንካችን እንደ ቨርቹዋል ባንኪንግ ማዕከል፣ የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት ፣ ንክኪ አልባ (Contactless cards) የክፍያ ካርዶችንና እንዲሁም የተለያዩ የዲጅታል የክፍያ ካርዶችን ለተጠቃሚዎች አስተዋውቋል፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ዘመናዊ አሰራሮች በተጨማሪ የሃገራችን የባንክ ቅርንጫፎች ከሚታወቁባቸው መደበኛ አሰራሮችና ገፅታቸው በተጨማሪ ዘመናዊና ተጨማሪ እሴት ለደንበኞች እንዲሰጡ ማድረግ ባደጉት ሃገራት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በመሆኑም ባንካችንም ይህንን አለምአቀፍ ተሞክሮ በመውሰድ ከተባባሪና አጋር ተቋማት ጋር ቅርንጫፎች ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ማዕከላት እንዲሆኑ ለማስቻል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
በዚህም መሰረት የዚህ ጥረት አካል የሆነውና ከጫካ ቡና ጋር በመተባበር ትናንት ስራ የጀመረው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት በካፌ በውስጡ በሚገኙ የኢንተርአክቲቨ ቴለር ማሽኖችና (ITM) የራስ አገዝ አገልግሎት መስጠት በሚችሉ ታብሌቶች አማካኝነት ደንበኞች ከቅርንጫፎች ማግኘት የሚችሉትን የባንክ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡
በተጨማሪም በማዕከሉ ውስጥ በሚሰጠው የካፌና የሬስቶራንት አገልግሎት ከጥሬ ገንዘብና ከወረቀት ንክኪ ነጻ (Cashless and Paperless) መልኩ በተለያዩ የዲጅታል አማራጮች የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈል ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ ማዕከል ለደንበኞች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ደንበኞችን የሚያረካ አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚታመን ሲሆን በቀጣይም ተመሳሳይ ማዕከላት በተመረጡ ስፍራዎች እንደሚከፈቱ በምርቃቱ ሥነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡
በመጨረሻም ጫካ ቡና ሃሳቡን ተረድቶ በአጋርነት ለመስራት ላሳየው ፈቃደኝነት አቢሲንያ ባንክ የተሰማውን ልባዊ ምስጋና አቅርቧል፡፡
Leave a Reply